Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, September 5, 2012

የጤፍ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናሩ ነዋሪዎችን አስግቷል

በታምሩ ጽጌ
ምክንያቱ ባልታወቀና ነጋዴዎችም ሲጠየቁ ምላሽ መስጠት ፈቃደኛ ባልሆኑበት ሁኔታ፣ የጤፍ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መናሩ ስጋት እንደፈጠረባቸው በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ ከወር በፊት አንድ ኩንታል ማኛ ጤፍ 1‚450 ብር ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ዋጋው በጣም አሻቅቦ 2‚100 ብር መሸጥ ጀምሯል፡፡ አንዳንድ ነዋሪዎች ጤፍ ከሚመረትበት ቦታ ወይም በቀጣይ የሚፈጠር ችግር እንዳለ በሚል ነጋዴዎቹን ሲጠይቋቸው፣ “ከፈለጋችሁ መውሰድ ትችላላችሁ አለበለዚያ ተውት” እንደሚሏቸው ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ቀለሟ ፈለቀ የሚባሉ ገበያተኛ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ውስጥ ነዋሪ ሲሆኑ፣ በየሁለት ወሩ ግማሽ ኩንታል ማኛ ጤፍ ይገዙ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ግማሽ ኩንታል ማኛ ጤፍ የገዙት 725 ብር ነበር፡፡ ሰሞኑን ወደ ደንበኛቸው መደብር ሲሄዱ ዋጋው ባልጠበቁትና በሚያስገርም ሁኔታ ጨምሮ 725 ብር ይገዙት የነበረው ማኛ ጤፍ ወደ 1,050 ብር አሻቅቦ ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡

ወቅቱ የበልግ ምርት የሚደርስበት በመሆኑ የተወሰነ የዋጋ ቅናሽ መደረግ ሲገባው ያለምንም ምክንያት መጨመሩ እንዳሳሰባቸው የገለጹት ወይዘሮ ቀለሟ፣ ምናልባት “እረኛና ነጋዴ የሚታየው ነገር ይኖራል” በሚል ፍራቻ 420 ብር ይሸጥ የነበረውን ግማሽ ኩንታል ሰርገኛ፣ ማኛ ጤፍ በሚገዙበት ዋጋ ሸምተው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ጤፍ በብዛት በሚሸጥባቸው ሾላ ገበያና አማኑኤል በረንዳ ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች እንደገለጹት፣ የጤፍ ዋጋ በተወሰነ መጠን ጨምሯል፡፡ ሸማቾቹ እንደሚሉት ግን የተጋነነ አይደለም ይላሉ፡፡ ክረምት በመሆኑና ከአምራቾች የሚመጣው ምርት በመቀነሱ በኩንታል ከሁለት መቶ ብር ያልበለጠ ጭማሪ ተከስቷል በማለት ያስረዳሉ፡፡ ማኛ አንደኛ ጤፍ በኩንታል 1,700 ብር ድረስ ይሸጣል ነው የሚሉት፡፡ ምናልባት አንዳንድ በመኖሪያ አካባቢዎች የሚገኙ ሽያጭና የወፍጮ ሥራ የሚሠሩ ነጋዴዎች ሊያስወድዱ ስለሚችሉ፣ ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው ለሚገኙ የወረዳ ወይም የክፍለ ከተማ አስተዳደርና ለፖሊሶች በመጠቆም ሕገወጥነትን መከላከል እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ቀለሟ ሁሉ ሌሎች ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ በርካታ የሰብል ምርቶች ማለትም ስንዴ፣ ገብስ፣ ዱቄት፣ ምስር፣ ለሽሮ የሚሆኑ ጥራጥሬዎች ሳይቀሩ የተወሰነ ዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡ በጤፍ ላይ ግን በጣም የተጋነነና “ምን ተፈጠረ?” የሚያስብል ጭማሪ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የጤፍ ዋጋ ንረት ያሰጋቸው ሰዎች ከነጋዴዎቹ ምላሽ በማጣታቸው ለወረዳ ኃላፊዎች ባደረጉት ጥቆማ አንዳንድ መደብሮች ቢታሸጉም፣ በምን ምክንያት እንደሆነ ሳያውቁ በሚቀጥለው ቀን መደብሮቻቸውን ከፍተው በጨመሩት ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

“ከባድ ጦርነት ሲኖርና ድርቅ መኖሩ ሲነገር ብዙ ሸቀጦችና የእርሻ ምርቶች ይወደዳሉ፤” በማለት የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች፣ በአሁኑ ጊዜ ምንም ችግር በሌለበትና ፈጣሪም የተስተካከለ ዝናብና ምርት እየሰጠ ባለበት ጊዜ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች፣ ሕገወጥ በመሆናቸው  ቅጣት ተጥሎባቸው ዋጋቸውን እንዲያስተካክሉ ማድረግ የሚጠበቀው ከአስተዳደሩ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በጤፍ ላይ የተደረገው ምክንያት አልባ ጭማሪ በአስቸኳይ የማስተካከያ ሕጋዊ ዕርምጃ ካልተወሰደበት፣ ቅጥ ያጣው የግብይት ሥርዓት የበለጠ ዜጎችን ለችግር ይዳርጋል የሚሉ አሉ፡፡ የኑሮ ውድነቱ ሸክም የብዙዎችን ሕይወት እያጎሳቆለ ምክንያት አልባ ጭማሪ ሲመጣ መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጀ ካልወሰደ ዜጎችን ማን ይታደጋቸዋል ሲሉም አበክረው ይጠይቃሉ፡፡

ነዋሪዎቹ በተፈጠረው የጤፍ ዋጋ ንረትና በሌሎች ሸቀጦች ላይ እየታየ ላለው የዋጋ ጭማሪ ምክንያቱን እንዲያብራሩልን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሽሰማ ገብረ ሥላሴን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ደውለው ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ፣ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳካልንም፡፡ 

No comments:

Post a Comment