Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, April 11, 2012

የሸራተን አዲስ ሠራተኞችና ማኔጅመንት አለመግባባት ተካሯል

 BY Ethiopian Reporter

በ2002 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ በሸራተን አዲስ ማኔጅመንትና ሠራተኞች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው ውዝግብ፣ አሁንም መቀጠሉን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የሠራተኛ ማኅበር ከተቋቋመ በኋላ ሠራተኞች ቀደም ሲል ያገኙት የነበረውን ጥቅማ ጥቅም በመቀነስና አንዳንዱንም በማቆም የሆቴሉ ማኔጅመንት በደል እንዳደረሰባቸው በመግለጻቸው፣ በከፍተኛ ሁኔታ የነበረውን አለመግባባት አቶ አብነት ገብረ መስቀልና የሕግ ባለሙያው አቶ ተካ አስፋው ጣልቃ በመግባት ነገሩን ማርገባቸው ይታወሳል፡፡


በመሆኑም ማኔጅመንቱና መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበሩ
ባደረጉት ድርድር ስምምነት ላይ በመድረሳቸው፣ እ.ኤ.አ ማርች 21 ቀን 2011 የኅብረት ስምምነት በመፈራረም፣ የተስማሙባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች አንቀጽ በአንቀጽ በመጥቀስ ለሠራተኛው መደረግና መከበር የሚገባቸውን መብቶች፣ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆኑ ተስማምተው እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሠራተኞችና ማኔጅመንቱ የኅብረት ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ፣ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ እንዲሆን በሚል የሠራተኛ ማኅበሩ አንድ ዝግጅት በማድረግ ለማኔጅመንቱ ኃላፊዎች፣ ለሆቴሉ ቅርብ ሰዎችና ለውጤታማ ሠራተኞች ሽልማት በማዘጋጀት መሸለሙን፣ በመቀጠልም የማኅበሩ ተወካዮችና የማኔጅመንት አባላት ተከታታይ ውይይቶችን ማድረጋቸውን፣ የማኅበሩ ተወካዮች ለሠራተኞቹ ሥራቸውን እንዴት መሥራት እንዳለባቸው፣ የሆቴል ሥነ ሥርዓትና ሌሎች ሥልጠናዎችን ከ50 ሰዓታት በላይ መስጠታቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ነገር ግን የሆቴሉ የማኔጅመንት ኃላፊዎች ከሠራተኞች ጋር ስምምነት ፈጥረውና በስምምነታቸው መሠረት የሠራተኞችን መብት ማክበር ሲገባቸው፣ በተቃራኒው በትንሽ በትልቁ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ደመወዝ መቀነስ፣ ከሆቴሉ ባለቤት ይሰጥ የነበረውን ጉርሻ ማስቆም፣ ተቆጣጣሪዎች ላለፉት 14 ዓመታት ይሰጣቸው የነበረውን የትራንስፖርት አበል አለመክፈል፣ የደመወዝ እርከን መከልከልና ሌሎች በደሎችንም መፈጸም ተግባራቸው ማድረጋቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበሩ በሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን አግባብ ያልሆነ የመብት ረገጣ በመቃወም የማኅበሩ ተወካዮች እ.ኤ.አ ዲሴምበር 26 እና 27 ቀን 2011 ከድርጅቱ የሰው ኃይል አስተዳደርና ረዳት አስተዳደር ጋር ተወያይተው እንደነበር፣ የሆቴሉን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ ከሆቴሉ ማኔጅመንት ጋር ጃንዋሪ 3 ቀን 2012 በድጋሚ ውይይት በማድረግ ማኅበሩ ያቀረባቸውን ነጥቦች ትክክለኛነት ተረጋግጦ፣ በአንድ ወር ውስጥ ለመፈጸም ቢስማሙም ተፈጻሚ ሊሆን አለመቻሉን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበሩ ከዓመት በፊት ማኔጅመንቱ ለመፈጸም የተስማማባቸውን ዘጠኝ አንቀጾችን በመጥቀስና ተፈጻሚ ያልሆኑ አምስት አንቀጾችን በማስታወስ፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 1771 እና 1776 መሠረት የሕግ ማስጠንቀቂያ መጻጻፉን፣ ተግባራዊ ካልተደረገለትም በሕግ የሠራተኛውን መብት ለማስከበር የሚገደድ መሆኑን እንዳስታወቀ ምንጮቹ አብራርተዋል፡፡

የሸራተን አዲስ የሰው ሀብት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤድና ታሞንዶንግ መጋቢት 18 ቀን 2004 ዓ.ም. ለሠራተኛ ማኅበሩ በጻፉት ደብዳቤ፣ ምንም የተጣሰ የኅብረት ስምምነት አንቀጽ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ከሰባት የማያንሱ አንቀጾች ተግባራዊ መደረጋቸውንና የደመወዝ ጭማሪ ጥናትን ጨምሮ ቀሪዎቹንም ተግባራዊ ለማድረግ በሒደት ላይ መሆናቸውን ማስታወቃቸውን፣ ከሆቴሉ ማኔጅመንት ኃላፊዎች አካባቢ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ወ/ሮ ኤድናን በስልክ ለማግኘት በተደረገው ሙከራ “እኔ ለሚዲያ መግለጫ ለመስጠት ኃላፊነቴ አይፈቅድም፤” የሚል ምላሽ በጸሐፊያቸው በኩል ሰጥተዋል፡፡ የሸራተን አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዦንፔር ማኒጎፍን ለማግኘት ተሞክሮ “ስብሰባ ላይ ናቸው፤ ሲጨርሱ እደውላለሁ፤” የሚል ምላሽ ከጸሐፊያቸው ቢገኝም፣ ለሕትመት እስከተገባበት ሰዓት ድረስ ምላሻቸው ሊገኝ አልተቻለም፡፡ እንደገና ቢደወልላቸውም “ወጥተዋል” በመባሉ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment