Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Monday, April 9, 2012

የአማራ ህዝብ ሁኔታ በህወሃት የአገዛዝ ዘመን

By መስፍን አማን

ሰሞኑን በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ጉራፋርዳ በተባለ ወረዳ የሚኖሩ በርካታ የአማራ ተወላጆች ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናችሁ በሚል እስከ የካቲት 30 ቀን 2004ዓ.ም ድረስ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላልፎባቸው ከአካባቢው በሃይል መፈናቀላቸውን በዜና መዘገቡ ይታወቃል። አንዳንድ ወገኖችም ለቻይናና የህንድ ዜጎች መሬት የማግኘት ያልተገደበ መብት በተሰጠባት ሃገር በገዛ ሃገራቸው ከአንድ ክልል ወደሌላ ክልል በመሄድ መሬት በማልማት መኖር የጀመሩ ወገኖችን ክልላችሁ ስላይደለ ወደቦታችሁ ተመለሱ መባሉ አስገራሚ እና አሳዛኝ ሆኖ አግኝተውታል። አምባሳደር እምሩ ዘለቀ የተባሉ አንጋፋ ዲፕሎማትና የሃገር ሽማግሌ የነገሩን አሳሳቢነት በማየት በድረገጾች የመወያያ ወድረክ ላይ የችግሩን አደገኛነት በማውሳት አስተያየታቸውንም ጽፈዋል። እርግጥ ድርጊቱ ላለፉት 21 ዓመታት ተደጋግሞ የተከሰተና ብዙ ያስባለ ጉዳይ ነው። ለምን ይህ ይሆናል? ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አስፈላጊና ለሚመለከተው ሁሉ ግልጽ መደረግ አለበት ባይ ነኝ።ድርጊቱን የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ና አመራሮቻቸው ያስፈጽሙት እንጂ፣ ህወሃት የሚቆጣጠረው ፌደራል መንግስት ሳያውቅ የተፈጸመ እንዳልሆነ ከዚህ ቀደም የሆነውን በመተንተን አንድ ሁለት ብሎ መረጃ በመጥቀስ ማረጋገጥ ይቻላል። ለዚህ ነው፣ ክስተቱ እንግዳ የሆነ ዱብዳ ነገር ሳይሆን፣ እንዳውም እቅድ ተይዞለት ፖሊሲ ወጥቶለት የሚፈጸም ተግባር ነው የምለው።ከፋሺስት ኢጣልያን ጀምሮ፣ የዚህና የዛ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ነን እስከሚሉ ቡድኖች ድረስ ሞክረውት ያልተቋጨ ተልእኮ እንጂ። 

የቤንች ማጂ ዞኑ ክስተት እንደ መነሻ አነሳሁት እንጂ የዚህ ጽሁፍ አላማ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት/ወያኔ) በተለይ የአማራውን ህብረተሰብ በተመለከተ የሚከተለውን ፖሊሲና የሚፈጽመውን ድርጊት፣ መቃኘት ነው። ከተመሰረተ ወደ አራት አስርት አመታትን ለማስቆጠር ምንም ያልቀረው ይህ ቡድን፣ በታሪክ አጋጣሚ እድል ቀንቶት የሃገሪቱን መንበረ ስልጣን ከተቆጣጠረ እንዲሁ 21 ዓመታት ማስቆጠሩ ይታወቃል። ይህ ዘመናዊ የትግራይ ብሄረተኝነትን የሚያቀነቅን ቡድን መሰረቱ ዘመነ መሳፍንትና ከዛ ወዲህ የሰሜንና ማእከላዊ የኢትዮጵያ መሳፍንቶች ያካሄዱት ክልልና አውራጃ ላይ የተመሰረተ የስልጣን ሽኩቻ ትግል ውርስ እንደሆነ የሚታወቅ ነው።የአሁኑን ለየት የሚያረገው በማርክሲዝም ርእዮተ ዓለም የተሸፈነ ዘረኛ የሆነ ጸረ-ሃገር ቡድን መሆኑ ላይ ነው። በትግራይ ብሄረተኞች የተመሰረተው ይህ ቡድን ባወጣቸው ማኒፌስቶዎች፣ ፕሮግራሞች እና ሌሎች መግለጫዎች፤ አማራንና የአማራን ህዝብ ሳይከስ፣ ሳይኮንን ያለፈበት ግዜ የለም ብንል ከእውነት ጋር አንቃረንም። 

የጥላቻ ጥንስስ

ግንባሩ በግልጽ በሚያወጣቸው ጽሁፎች አንዳንድ ግዜ ‘የገዢ መደብ’ የሚል ተውላጠ-ስም ቢታከልበትም ባካሄዳቸው እንቅስቃሴዎች አማራን እንደ ህዝብ የሚያጥላሉ መጣጥፎች፣ መዝሙሮች፣ ሽለላዎችና ድራማዎችን ይጠቀም እንደነበረ ቀደምት አባላቶቹ ሳይሸሽጉ የሚናገሩት ሃቅ ነው። ነገሩን በጥልቀት ለተመለከተ፤ ድርጅቱ ይህንን ተግባር የሚፈጽመው በስህተት ወይንም አባላቱ በሚፈጽሙት የዲሲፕሊን ግድፈት ሳይሆን፣ እንዳውም የአማራውን ህዝብ በስትራቴጂክ እና ታሪካዊ ጠላትነት ፈርጆ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ስለመሆኑ ብዙ ብዙ ማስረጃዎችን ለማቅረብ መድከም አያሻም። ድርጅቱ ትግሉን ገና ‘ሀ’ ብሎ ሲጀምር “አማራና ኢምፔሪያሊስምን”በትግራይ ህዝብ ደመኛ ጠላትነት ፈርጆ እንደሆነ በወቅቱ የነበሩ ሁሉ የሚያስታውሱት ነው።

ማህበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ (ማ.ገ.ብ.ት) የተባለውን የወያኔ እርሾ ስብሰብ ለመጀመር መነሻ የሆነው በአንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የተበተነው ጽሁፍ፤ “…የኢትዮጵያ ስልጣኔ መሰረት የሆነው የትግርይ ብሄር በተከታታይ የመጡ የአማራ አገዛዞች እስከፊ ለሆነ የብሄር ጭቆናና የከፋ ድህነት ውስጥ እንዲወድቅ ማድረጋቸውን…” (ማገብት፡ 1967) በመግለጽ የትግራይን ብሄር በደልና ጥቃት በማዛባት ቅስቀሳውን አንድ ብሎ ጀምሮአል። ወያኔ ከተመሰረተ በኋላም በድርጅቱ  ተዘጋጅቶ ሱዳን ሃገር ታትሞ የወጣው ማኒፌስቶ 68 በመባል የሚታወቀው ሰነድ፤ “ለትግራይ ሁዋላ ቀርነትና ችግር ተጠያቂው የአማራው ገዢ መደብና፣ ከእርሱ በሚገኝ ፍርፋሪ ተጠቃሚ የሆነው የአማራው ህዝብ ነው..” (ትህነድ፡ የካቲት፣ 1968) ሲል በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጧል። ከዛም በኋላ ድርጅቱ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና ቅስቀሳዎች ስልጣን ላይ ከነበረው ወታደራዊ ደርግ ይልቅ፣ አማራን እንደ ጠላት ኢላማ ያደርጉ እንደነበሩ በወቅቱ ያሰራጩዋቸው ከነበሩ በራሪ ወረቀቶች መረዳት ይቻላል።ለሽለላና ቅስቀሳ ይውሉ ከነበሩ ታዋቂ አባባሎቻቸውም መሃከልም ፤ ”ገረብ ገረብ ትግራይ መቃበረ አምሃራይ!” ወደ አማርኛ ሲመለስ ‘የትግራይ ሸለቆዎችና ኮረብቶች የአማራ መቀበሪያ ይሆናሉ!’ የሚሉትንም እናገኛለን። 

ለቡድናቸው በተለያየ ጊዜ የተለያየ ስም በመስጠት (ማኅበረ ተጋሩ፣ ማግብት፣ ግንባረ ገድሊ ትግራይ፣ ተሐሕት፣ ሕወሐት) አሁን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት ተብሎ የሚታወቀው ድርጅት የተጣመመ የዘረኝነት ቅስቀሳ በማካሄድ ሕዝቡ በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፣ በተለይም በአማራው ላይ ጥላቻና ቂም እንዲቋጥር አድርገዋል። “የወያኔው ታላቅ ሤራ በቀድሞው አባላቱ ሲጋለጥ” (1982 ዓ.ም) በሚል ርዕስ በወጣ አንድ መጽሃፍ ላይ በአቶ አብርሃም ያየህና በአቶ ገብረ መድህን አርአያ በስፋት ቀርቧል። በዚሁ መጽሃፍ ድርጅቱ የትግራይን ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ በመክተት የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ ሌት ተቀን ይሰራ እንደነበር፣ አቶ አብርሃም ያየህ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡

“ለምሳሌ አሁን ይዤው ባልመጣም በድራማ መልክ ለቅስቀሳ የተዘጋጀ አንድ ካሴት  ግንኙነት    ሲያደርጉ ‘አማራ ከሆነ እንዳትለቀው ፈሪ ነው’ ሚል ቃል ሲገኝበት በቪዲዮና በካሴት የተቀረጹ ዘፈኖቻቸውም ቢሆኑ “አማራ ገዢዎቻችን” የሚሉ ጠባብ ብሄረተኝነትንና ጥላቻን የሚነዙ ነበሩ” (የወያኔው ታላቁ ሴራ በቀድሞው አባላቱ ሲጋለጥ፣ 1982 ዓ.ም. ገጽ 16-17) 

አቶ አብርሃም በማከልም ዘፈኖቻቸውና በራሪ ወረቀቶቻቸው ጸረ-አማራ ቅስቀሳ ያራምዳሉ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ የሚፈለገው እርስ በርሳችን እንድንተላለቅ ነው በማለት ስጋቱን በጊዜው ገልጿል። ሌላው እና ከህወሃት መስራቾች አንዱ የሆነው ፣ አረጋዊ በርሄ ለዶክትርና ማሟያ በጻፈው መጽሃፍ፣ ድርጅቱ በ1979 ዓ.ም. (የፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር መሆኑ ነው) አካሂዶት ከነበረው ጉባኤ በኋላ አማራን እንደ ህዝብ የሚያጥላሉ ቅስቀሳዎች ይበረታቱ እንደነበር እንዲህ በማለት ይገልጸዋል ፡

The 1979 TPLF Congress adopted a new programme, devised to correct the secessionist trend that had started to creep into the organization. Yet it would not be far from the truth to say that the TPLF did not explicitly attempt to struggle for a united and democratic Ethiopia during the period between the organization’s first and second congresses. Contrary to its publicly stated objective, anti-Amhara propaganda was subtly encouraged within the movement. Cultural events, theatrical performances as well as jokes and derogatory remarks were used to disseminate this poisonous attitude. Fuelling some historical grudges perpetrated by the ruling classes, the Sibhat faction tried to cast doubt on the possibility of living in unity with ‘the Amhara’. (A political History of Tigrai people’s liberation Front፣ page 163)

 “ኢ.ሕ.አ.ሠ*. (የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ሠራዊት) ከ1964-1970″ በተሰኘው የአስማማው ኃይሉ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ የሚከተለውን እናገኛለን ፡ “…ከቀጠሮው ቀን በፊት የተወሰኑ የተሐሕት ሠራዊት አባላት አሲንባ አካባቢ ሐረዘ ከሚባለው መንደር ሕዝብን ሰብስበው ‘አማሮችን’ እንደሚያስወጡ ገለፁ።” ገጽ 237. አክሎም “የሕወሐት አባላት ከኢ.ሕ.አ.ሠ ጋር የሚታገሉትን የትግራይ ተወላጆች ‘ኩርኩር አምሐሩ’ (የአማራ ቡችላዎች).. በማለት ይሰድቧቸው ነበር።” (ገጽ 192.) በማለት ጽፎአል። አቶ ገብረ መድህን አርአያ የተባለው ሌላው የወያኔ የቀድሞ ፋይናንስ ክፍል ሃላፊ፣ በባህል ክንውኖች፣ ትያትሮችና የመዝናኛ ዝግጅቶች በአማራ ህዝብ ላይ መርዘኛ እና አጸያፊ የሆኑ ቀልዶች፣ አባባሎች ይነገሩ ነበር፣ በማለት እንዲያውም በታሪክ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶችን በማጋነን አክፍቶ በማቅረብ ከአማራ ጋራ መኖር እንደማይቻል ይሰበክ ነበር ብሏል።

 ለባእዳን የሚደረግ ጸረ-አማራ ቅስቀሳ

 ይህ በዘረኝነት ልክፍት የተሳከረ ድርጅት የትግራይ ህዝብ ብቸኛ ወኪልና ጥቅም አስጠባቂ መሆኑን በመለፈፍ፣ አማራው የዚህ ተልእኮ እንቅፋት እንደሆነ ከሃገር ቤት አልፎ በውጭ ሃገራት ለሚገኙ ደጋፊዎቹና ባእዳን ጭምር ይቀሰቅስ እንደነበርም የአደባባይ ምስጢር ነው። ስልጣን ላይ ከመውጣቱ አንድ አመት አስቀድሞ ከApril 3 እስከ 5 ፣1990ዓ.ም. እኤአ መለስ ዜናዊ የCIA ባልደረባ ከነበረው ፖውል ሄንዝ ጋር ዋሽንግተን በሚገኘው የህወሃት ጽ/ቤት በሁለት ዙር አምስት ሰዓታት የፈጀ ውይይት አድርጎ ነበር። በዚህ ውይይት መሃል ስለ አማራ የተናገረውን ቀንጭበን ብናይ የሚከተለውን እናገኛለን፡

PBH: What do you mean by AMHARA domination? If this is your message, how do the people in the regions where you have recently advanced – - Lasta, Gaynt, Saynt, Manz, Merhabete, etc., all of which are inhabited predominantly by Amhara – - look on your movement? MZ: These Amhara are oppressed people. When we talk about Amhara domination, we mean the Amhara of Shoa, and the habit of Shoan supremacy that became established in Addis Abeba during the last hundred years. This system has to change. The people who think they have a right to dominate in Addis Abeba have to change their mentality. This is the mentality the Derg adopted from the very beginning. No people of Ethiopia have the right to dominate any other.(http://addisvoice.com/2011/06/paul-henzes-coversations-with-meles-zenawi/)

ስልጣንን በፈላጭ ቆራጭነት ተቆጣጥሮ ሃገሪቱን በብቸኝነት የሚያሾረው መለስ ዜናዊ ከውጭ ሰዎችንና ዲፕሎማቶች፣ ተቃዋሚዎቹን በተመለከተ ለሚቀርብለት ጥያቄ የዘወትር መልሱ “ተቃወሞ የሚያሰሙት ስልጣናቸውን ያጡና የድሮ ጥቅም የቀረባቸው አማሮች ብቻ ናቸው” እንደሚል በአንድ ወቅት በስራ ምክንያት ያወቅኩት አዲስ አበባ የሚገኝ የምእራብ ሃገር ዲፕሎማት አጫውቶኛል። ይህው ዲፕሎማት ገዢ የሚባለው የአማራ ህብተረሰብ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማየት በአንዳንድ የአማራ አካባቢዎች ቅኝት አድርጎ ሲመለስ፣ የብዙሃኑ አማራ ገበሬ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ከሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ባነሰ የእድገትና የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በሃዘኔታ ገለጾልኛል። 

ከአማጺነት ወደ ‘መንግስት’ ሥልጣን

ሶቪየት ኅብረትና የሶሻሊስቱ ጎራ በመንኮታኮቱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት በመማረሩና የነበረው መንግሥት በሁለት እግሩ መቆም ባለመቻሉ ይህ ቡድን በግንቦት ወር 1983ዓም የሀገራችንን ስልጣነ መንግስት በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ በቃ። ይሁን እንጂ ከዚህም በሁዋላ ቢሆን በአማራው ህብረተሰብ ላይ ያለው የበቀልና የጥላቻ ፖሊሲ መጨመር እንጂ መቀነስ አልታየበትም።

የሽግግር ጉባኤ ተጠርቶ የብሄር እና የጎሳ ልሂቃን በየብሄራቸው በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ሲደረግ፣ ከሃገሪቱ ህዝብ ብዛት ሲሶ የሚሆነው የአማራን ማህበረሰብ የሚወክል አካል አለመኖር በወቅቱ አነጋጋሪ እንደነበር አይረሳም።የመርህ ጉዳይ ነው እንዳይባል ኢህአፓን በጦርነት አስወግዶ ትግራይ አካባቢ በምርኮ ያስቀራቸው ምርኮኞች፣ ጓዶቻቸውን ለፈጀው ቡድን እጃቸውን ሰጥተው በሎሌነት ለማገልገል ቢወስኑም ትግሬዎች ባለመሆናቸው ወያኔ ከራሱ ጦር ጋር ለመቀላቀል የዘር መርሆው ስለማይፈቅድለት ለጊዜው አግልሎ አቆይቷቸው እንደነበር የሚታወቅ ነው። በተፈጥሮ መሠሪ የሆኑት የወያኔ መሪዎች፣ በአገልጋይነት ለማደር እስከቀረቡ ድረስ በቁጥጥራችን ሥር አድርገን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ማወናበጃ እንጠቀምባቸው በሚል ኢ.ሕ.ዴ.ን (የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በሚል የድርጅት ታርጋ እንዲታቀፉ ተደረጉ። በኋላም መ.ዐ.ሕ.ድ ማለትም (የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት) የዐማራውን ሕዝብ ሰቆቃ ለመታደግ ተቋቁሞ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ንቅናቄ በመጀመሩ እና ለወያኔም ስጋት እየሆነ በመምጣቱ እነዚህን ወዶ ገቦች ብ.አ.ዴ.ን. ማለትም (የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) የሚል ሌላ ስም በመስጠት የአማራ ድርጅት እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል። የብአዴን ዋነኛ ስራ አማራውን መቆጣጠርና ማኮላሸት እንደሆነ ብዙ ስለተባለለት እዚህ ጋር ግዜ አላጠፋበትም። 

ሌላው የሽግግር መንግስት ወቅት ወያኔ በተቆጣጠራቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተቀሩት ብሄሮች በአማራ ህዝብ ላይ እንዲነሱ የቀን ከሌት ቅስቀሳ ይካሄድ እንደነበር ከዛን ግዜ ትውስታዎቻችን ውስጥ አንዱ ነው። እንዳውም አንዳንድ የወያኔ መሪዎች ኢህአዴግ የመጣላቸውና የመጣባቸው ህዝቦች አሉ እስከማለትም ደርሰው ነበር። ይህ የወያኔ ፍላጎትም ውጤት ማሳየት ጀምሮ፣ በሐረር ከተማ የሆነውን እዚህ ጋር ማስታወሱ አግባብነት አለው። ወቅቱ ከወያኔ በተጨማሪ በአካባቢው በጃራ-አባገዳ የሚመራው እንደ አይ.ኤፍ.ኤሎ (IFLO) መሰል ድርጅቶች ታጣቂቹን አሰማርቆ ይንቀሳቀስ ነበር። ድርጅቱ ከሐረር ወጣ ብሎ የሚገኝ አነስተኛ ከተማን የጥቃት ኢላማው በማድረገ፣ከተማዋን ለሳምንታት በመክበብ ምግብና ቁሳቁስ በመከልከል ህዝቡን ለመፍጀት ሲሰናዳ፣ በሐረር ከተማ የሚኖሩ ይህን የሰሙ ዜጎች በሰላማዊ ሰልፍ በወቅቱ የምስራቅ እዝ አዣዥ ለነበረው የዛሬው ኢታማጆር ሹም ሳሞራ የኑስ አቤቱታቸውን ያሰማሉ። የሰልፈኞቹ ተወካይ ሆነው መልእክት ለማድረስ ከገቡት ወገኖች መሃከል (በሰራ ምክንያት የተዋወቅኩት ወጣት) ሳሞራ የሰጣቸው መልስ ያልጠበቁት ብቻ ሳይሆን ምን ግዜም እንደማይረሳው ተርኮልኛል። ለሰልፈኞች መልእክተኞች የሽግግር መንግስቱ ተወካይ፣ የሳሞራ ይኑስ መልስ አጭርና ግልጽ ነበር “ነፍጠኞች ናቸው፡ ይበሉዋቸው” በማለት ከቢሮው እንዲወጡ አሰናበታቸው። 

ድርጅቱ በአማራው ላይ የሚከተለው ስር የሰደደ የጥላቻ እና የበቀል ፖሊሲ ሌላው መገለጫ አንዳንድ የአካባቢና የክልል ፖለቲከኞች ሹመትም ሆነ ሌላ ጥቅምን ሲሹ አማራን እንደሚጠሉ ለጌቶቻቸው ወያኔዎች ማሳየት እንደ የሹመት ማግኛ ስልት ሆኖ ማገልገሉ ነው።ታምራት ለአይኔ ጂጂጋ ከተማ ለተሰበሰቡ የኦጋዴን ሶማሌ ተወካዮች “ገዜው የእናንተ ነው፣ አንገታቸውን አስደፉቸው” እስከማለት ደርሶ የነበር ሲሆን።ሃሰን አሊ ከአንድ የገጠር መምህርነት አልፎ ለክልል ፕሬዚዳንትነት የበቃበት ትልቁ ችሎታው በየመድረኩ ለአማራ በሚያሳየው የጥላቻ ንግግር ነበር። የህገ-መንግስት ጉባኤ በተባለው ስብሰባ ላይ አንድን ህዝብ ሲዘልፍና ሲያንጉዋጥጥ፣ በአዳራሹ የነበሩት የህወሃት ሰዎች በደስታና ሳቅ ሲፍለቀለቁለት፣የተቀረው የጉባኤ ተሳታፊ በጭብጨባ ሲያጅበው በቴሌቪዥን መስኮታችን ተመልክተናል።በአርባ-ጉጉው እልቂት ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሆነው የኢህአዴግ-ኦህዴድ የአካባቢው ተጠሪ ዲማ ጉርሜሳ ለፈጸመው ጸረ-አማራ ተግባር ወያኔዎች በሹመት ላይ ሹመትን አከናንበውታል።

 በተቀሩትም የብሄርና ክልል ድርጅቶች ዘንድ ወያኔ አማራውን እንደ ጠላት በመሳል ከዚህ በፊት በሃገሪቱ ለደረሱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጭምር ተጠያቂ ማድረጉን የተለመደ የፖለቲካ ተግባሩ አድርጎ ይዞታል። እንዳውም አንድ እንቅስቃሴ በታየ ቁጥር “አማራ መጣላችሁ” እና የመሳሰሉ ጥሪዎች በወያኔ ተዘውትረው ጥቅም ላይ የሚውሉ የቅስቀሳ ስልቶች ናቸው። ምርጫ 97ን ተከትሎ የተፈጠረውን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለማምከን ‘ነፍጠኛው መጣላችሁ’፣ እና ‘በትጥቅ ትግል የጣልነው የአማራ ስርአት በምርጫም ቢሆን አይመረጥም’ የሚሉ ቅስቀሳዎችን ሲጠቀሙ እንደነበር የቅርብ ግዜ ትውስታችን ነው። የዚህ አይነቱ ቅስቀሳ አይነተኛ ማስረጃ የሚሆነው ድምጸ ወያኔ የተባለው ራዲዮ በትግራይና አካባቢዋ ያስተላልፍ የነበረው እልቂት ጠሪ ቅስቀሳ ነበር። እንዳውም ከምርጫው በሁዋላ ገዢው ፓርቲ ለካድሬዎቹ  ባሳተመው መጽሃፍ (ዴሞክራሲና አንድነት በኢትዮጵያ፣ ነሐሴ 1998ዓም)፣ አማራውን “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብና ስርአት ጸር ነው” ሲል በግላጭ ፈርጆታል። በወቅቱ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ በተደረገው ውይይት ይህ የገዢው ፓርቲ አቋም የተንጸባረቀ ሲሆን፣ እንዳውም አዋሳ ላይ በተደረገ አንድ የካድሬዎች ስብሰባ ተፈራ ዋልዋ “አማራና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የዴሞክራሲያችን ጠላቶች ናቸው” እንዳለ የምናስታውስ አለን።

 “የትግራይ ህዝብና የትምክህተኞች ሴራ” በሚል ርእስ (1999ዓም) ገብረኪዳን ደስታ በተባለ ግለሰብ የተጻፈው መጽሃፍ ወያኔዎች በጋራ ከምትገነባ ዲሞክራሲያዊት ከሆነች ሃገርና ፍትሃዊ ስርአት ይልቅ የሚመኟት ትግራይም ሆነ ኢትዮጵያ ምን እንደሆኑ ቅልብጭ ባለ ሁኔታ አስቀምጧል።

 “ብሄረ ትግራይ የባህል፣ የታሪክ፣ የአንድነት፣የጀግንነት፣የመቻቻል፣የእኩልነት፣የአልበገር ባይነትና የኢትዮጵያ ህዝብ ስልጣኔ እምብርት እንደሆነች ሁሉ፣ ካብያ ነበረነሰ እኒህኒ፣ነውና ዛሬም ያለፈውን ታሪክ ለመድገም የስራ፣የባህል፣የእውቀት፣የምርምር፣ የአንድነት፣የእድገትና የብልጽግና ማእከል ሆና መቀጠል ይኖርባታል።እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ ሳይሆኑ ከቀሩ ግን፣የትግራይ ህዝብ የአመታት ተጋድሎ፣ ጀግኖች በከፈሉት ክቡር መስዋእትነት የተጎናጸፍነው ብሄራዊ እኩልነትና ሃገራዊ አንድነት ለትግራይ ደመኛ ጠላቶች መጋለጡ አይቀርም። (ገጽ 10)

ሲል ወያኔዎች ያላቸውን አቋም ደመኛ ጠላቶቻችን በሚሉ መርዘኛ ሃረጎች ጽፏል። ይህንኑ የገብረ ኪዳን ደስታ አባባል ሳይጨምር ሳይቀንስ መለስ ዜናዊ በየካቲት ወር 2002 ዓም በተከበረው 35ኛ አመት የድርጅቱ ምስረታ በዓል ላይ እንዲህ በማለት ደግሞታል “ስለሆነም እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶቻችን አሁን እኛን በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ዕጦት ቢወቅሱን የሚያስገርም አይደለም። የትግራይ ህዝብ ታግሎ የጣላቸው ደመኛ ጠላቶች እንደገና ዛሬ መልሰው ለማምጣት ቢሞኩሩም ህዝቡ በጠላቶቹ ላይ ምንም ዓይነት ብዥታ ስሌለው ጠንክሮ ይታገላቸዋል እንጂ አይደነጋገርም።” ሲል መቀሌ አደባባይ ላይ ለተሰበሰበው ህዝብ ተናግሮአል። ይህ የጥላቻ ቅስቀሳ ምንያህል ስር በደሰደደ መልኩ እንሚገለጽ በዝርዝር ለመረዳት አለምሰገድ አባይ በ1998ዓም እ.ኤ.አ. ፡Identity Jilted or Re/Imagining Identity: The Divergent Paths of the Eritrean & Tigrayan Nationalist Struggles /Alemseged Abbay 1998/ የጻፈውን መጽሃፍ እንዲመለከቱ እጋብዛለሁ ። 

አዝጋሚ ዘር የማጥፋት ዘመቻ 

ወያኔ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በአማራው ህዝብ ላይ የፈጸማቸውን ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ድርጊቶች እንዘርዝር ብንል ግዜና ወረቀት ላይበቃን ይችላል። አለፍ አለፍ ብሎ አንዳንዱን ማየቱ ግን አይከፋምና እነሆ፣ 1983ዓ.ም. ኤርትራ ውስጥ የሶስት ነጻ አውጭ (ህወሃት፣ኦነግ እና ህግአኤ)ድርጅት መሪዎች ተገናኝተው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ገዢ የሆኑ ውሳኔዎችን አስተላለፉ። ከነዚህም ውሳኔዎች መሃከል ዛሬ እየተሰራበት ያለውን የፌደራል ክልሎችን አዋቅረው በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የክልል ድንበር አሰመሩ። በወቅቱ በነበረው የሃይል አሰላለፍ መሰረት አማራው በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ህዝብ መኖሩ ጥያቄ ላይ መውደቅ ብቻ ሳይሆን፣ ለህልውናውም ሆነ ጥቅሙ የሚቆረቆር አካል ባለመኖሩ ወልቃይት-ጸገዴ እና አንዳንድ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ለትግራይ፣ እንዲሁም በወቅቱ ሌላኛው የሽግግር መንግስት ባለድርሻ ኦነግ እወክለዋለሁ ለሚው ህዝብ እስከቻሉት ድረስ ክልል ከለሉ።ይህ ከላይ ወደታች የተፈጠረ የክልል ድንበር ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ በሃገሪቱ ብሄሮች አለመተማመንን መፍጠር ብቻ ሳይወሰን፣ለማያባራ ግጭት መንስኤ በመሆን እያተራመሰ እንዳለ ሁላችንም የአይን ምስክሮች ነን። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኝ በምርጫ 2002ዓም ቅስቀሳ ወቅት በትግራይ የተከሰተን አንድ ነገር እንመልከት። ህወሃት ከአረና ትግራይ የገጠመውን ፈተና ለመከላከል የሄደበትን ርቀት የአዲስ ነገር የተባለ ጋዜጣ ሪፖርት እንዲህ በማለት ዘግቦታል፣ “ህወሃት ፎቶኮፒ በማባዛት አረና የትግራይ መሬቶችን በሙሉ ለአማራ ክልል እንደሚመልስ ቃል መግባቱ በማተት በየከተማው ያሰራጫል። በፎቶ ኮፒ እየተባዙ የትም የሚለጠፉት እነዚህ ፅሁፎች ከአናታቸው እንዲህ የሚል ርእስ ይነበባል፡፡ “ሽያጢ ዓዱ ዝኾነ ዓረና ዝበሎ ጉድ ሰሚናዶ?” (አገር ሻጭ የሆነው ዓረና ያለውን ጉድ ሰምታችኋልን?)። ወረድ ብሎ እንዲህ የሚል አርስት ይገኛል፡-

“ኻብ ክልል አምሓራ ተቆሪሱ ናብ ክልል ትግራይ ዝእታው መሬት ናብ ዝነበሮ ክመለስ ክንግብር ኢና” ስየ አብረሃ፣ “ከአማራ ክልል ተቆርሰው ለትግራይ የተሰጡ መሬቶችን ለአማራ እንዲመለሱ እናደርጋለን” ስየ አብረሃ፡፡

 ዓረና በዚህ በባከነ ሰዓት በተከሰተው የህወሓት የቅስቀሳ ስልት ፍፁም በመደናገጥ፡ ማስታወቂያው በተለጠፉባቸው ግድግዳዎች ሁሉ እየዞረ ከያንዳንዱ ማስታወቂያ ጎን እንዲህ የሚል ማስታወቂያ ለጠፈ፡-”ለመላው የመቀሌ ነዋሪዎች በሙሉ-ዓረና ፓርቲ ከትግራይ ምንም አይነት መሬት የማስቆረስ አላማ የሌለው መሆኑን እንድትረዱልን እናሳስባለን” ክብ ማኀተም፡፡ (http://addisnegeronline.com/2010/05/) .

 

በአሁኑ ግዜ መሬት ወደትግራይ መከለልን በዝምታ የታለፈው አልበቃ ብሎ ከአፍሪካ በቆዳ ስፋቷ አንደኛ ለነበረችው ሱዳን መሬት ሳታጣ ጠፍ ከሆኑ የአማራ አካባቢዎች፣ ቤንሻንጉልንና ጋምቤላ ክልልን ጨምሮ በወያኔ ተመርቆላታል። ዊኪሊከሰ የተባለው የድረ-ገጽ መረጃ ምንጭ ይፋ ባደረገው የአሜሪካን መንግስት ውጭ-ጉዳይ መስሪያ ቤት የምስጢር መልእክት ልውውጥ መሰረት የመለስ መንግስት በዚህ የመሬት ስምምነት ከአማራ ክልል ሰፊ የሆነ መሬት ለሱዳን መተላለፉን እንዲህ ሲል አስነብቦአል “in the on-going tensions between Ethiopia and Sudan, Addis Ababa had turned over land to the Sudan which has cost the Amhara region a large chunk of territory” and tried to “sweep the issue under the rug.”(Check the Wikileaks Archive on Ethiopia.)

ወያኔ ምንም ከማድረግ እንደማይመለስ የቅርብ ግዜው ማሳያ በ2007ዓም የተካሄደው የህዝብ ቆጠራን የፖለቲካ መጫወቻ በማድረግ ከአማራው ህዝብ ቁጥር ላይ ወደ 2.5 ሚልዮን የሚጠጋውን መቀነሱ ነው።ነገሩን የበለጠ ለመረዳት ከዚህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ የሚገኙትን ሊንኮች/ዝርዝር ዘገባዎች ይመልከቱ።በተቀረው የሃገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው ስርተው እንዳይኖሩለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ ክልላችሁ አይደለም ተብለው የሚፈናቀሉ አማሮችን ዜና መስማት እየተለመደ በመምጣቱ እምብዛም አስደናቂ የማይሆንበት ደረጃ ላይ ተደርሶአል። ይህ የመፈናቀል ወሬ እንዳውም ባለፉት 21 ዓመታት ለአማራው ህብረተሰብ የዘወትር ገጠመኝ ሆኖአል።የሰሞኑን ዜና ጨምሮ ከዚህቀደም ተከሰቱትን ለማየት እንዲቻል ከዚህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ ያሉትን የድረ-ገጽ ሊንኮች/ዝርዝር ዘገባዎች መመልከት የሁኔታውን አስከፊነት ለመረዳት ይረዳል።

በጥላቻ የታወረ አመራር

አሁን ኢትዮጵያን እየመራ ያለው ወያኔ በአመራሩ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ከላይ ባነሳነው ጉዳይ ላይ ያላቸውን አተያይ እንመልከት። ከአውራው መለስ ዜናዊ ብንጀምር “አማራን አንገት ማስደፋት” የሚል አባባል እንዳለው በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ።የኢትዮ- ኤርትራን ጦርነት(1998-2001 እኤአ ዓ ም) መጀመር ተከትሎ የኤርትራው መሪ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ለአንድ የዐረብኛ መጽሄት በሰጠው ቃለ-ምልልስ “መለስ፣ የአማራ ፓራኖያ አለበት” ሲል የቀድሞው ትግል አጋሩን ገልጾታል። በነገራችን ላይ ፓራኖያ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የበረታ ጥላቻና ፍራቻ የሚል ትርጉም አለው።በቅርቡ የቀድሞ የአሜሪካን መንግስት የአፍሪካ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀርማን ኮህን ለኢሳት ከሰጡት ቃለምልልስ ውስጥ ስለ መሬት መሽጥ መለወጥ አስፈላጊነት አንስተው መለስ ዜናዊን ለጠየቁት ጥያቄ የሰጠው መልስ ከላይ የተነሳውን ሃሳብ የበለጠ የሚያጠናክር ነው፣ “መሬት እንዲሸጥ ካደረግን አማሮች ገዝተው ይጨርሱታል”  በማለት ነበር መለስ መልስ የሰጠው።

ሌላው የገነነ የአማራ ጥላቻ የተጠናወተው የወያኔ መሪ ስብሃት ነጋ ነው። ስብሃት ነጋ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአማራን ከማጥላላት ወደሁዋላ እንደማይል በቅርብ የሚያውቁት ይናገሩለታል። ከቅርብግዜ ወዲህም ስብሃት ብሶበት የአክሱም ስልጣኔ ደቡብ ትግራይንና የተቀረውን ኢትዮጵያን አይመለከትም በማለት በአደባባይ መናገር ጀምሮአል።የዘር ልክፍት በሽታ የተጠናወተው ስብሃት የጡረታ ግዜውን እንዲያሳልፍበት የተመደበበትን (Ethiopia International Institute for peace and development) የምርምር እና ቲንክታንክ ተቁዋም ከቆመለት አላማ ውጪ አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክን ለማጻፍ ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ እንዳለም ተሰምቶአል።

ቀድሞ የኢትኦጵ ጋዜጣ ባለቤት፣ ባሁኑ ወቅት የኢሳት ጋዜጠኛ የሆነው ሲሳይ አጌና በአንድ ወቅት ለንባብ ባበቃው ጽሁፉ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር፣ የሀገሪቱ የመከላከያ ሃይል አዛዦች ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከአንድ ብሄረሰብ የወጡ ብቻ ሳይሆኑ፣በህወሃት የጥላቻ ፖለቲካ የተጠመቁ 20 ዓመት የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች ሆነው፣ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው በአመለካከት የትግራይን ድንበር መሻገር ያቃታቸው እንደሆኑ የሚጠራጠር ቢኖር ለአብነቱ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ የተፈፀመውን ለምን አላስታውሳችሁም፤”በማለት ይጀምርና፣ “…በባንኩ የቦርድ አባላት ምርጫ በተፈጠረ አለመግባባት ብሄራዊ ባንክ ጣልቃ ይገባና ነሀሴ 15/2002 ከቀትር በፊት በባንኩ የስብሰባ አዳራሽ ስብሰባ ይጠራል፤በዚህ ስበሰባ ላይ ጄኔራል ሳሞራም በባለድርሻነታቸው ይገኛሉ፤ስብሰባው ከመጀመሩ ሳሞራ እጀቸውን ያነሳሉ፤ሲፈቀድላቸውም ቀጠሉ “ ‘ባለፈው የተመረጡት የት ሔደው ነው ሌላ ምርጫ የሚደረገው?ይህንን ባንክ ያቐቐምነው በታጋዮች የህይወት መስዋትነት እና አካላቸውን ባጡት የትግራይ ልጆች ደም ነው፤ቀደም ሲል ተካሄደው ምርጫ ውድቅ የሆነበት ቃለጉባኤ እንዲሰጠኝ ፈልጋለሁ፤ደርግን ከፍተኛ መስዋትነት ከፍለን ከስልጣን አውርደነዋል፤ አማራንም ዳግም እንዳይንሰራራ አድርገን አጥፍተነዋል’ ” ሳሞራ ይህንን ሲናገሩ አዳራሹ በጭብጨባ ደመቀ፤ ሌሎች ደንግጠውና ፈዘው ይመለከቱ እንደነበር ጽፎአል። http://www.ethiopianreview.com/amharic/?p=4829

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በአንድ ወቅት በግል የገጠመኝን እዚህ ላይ መጥቀሱ አግባብነት አለውና እነሆ። ግዜው 1993ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃወሞ አስተባብረሃል በሚል ክስ ታፍኝ ውደ ማእከላዊ ምርመራ በገባሁ ሶስተኛው ቀን፣ ተግባቢ አንዳንዴም አስፈራሪ ለሆነ መርማሪ ቃል እንድሰጥ ተደረገ። ብዙ ጥያቄዎችን አንዳንዴም ውይይቶችን አድርገን በመሃል ብሄርህ ምንድነው? የሚል ጥያቄ መርማሪየ አቀረበልኝ። የትውልድ ቦታየ አዲስ አበባ ሲሆን በአሁኑ የብሄር ምደባ ግን አማራ መሆኔን ስነግረው፣ “አባቶቻችሁ የገዙን አንሶ እናንተ ልጆቻቸው ትበጠብጡናላችሁ!፣” በማለት ስሜቱን መቆጣጠር እስኪሳነው የስድብ ውርጅብኝ አወረደብኝ፤ “አታስቡት ተያይዘን እንጠፋፋለን” አለኝ። የተለመደውን ዱላና ማስፈራራት ቀምሼ ምርመራውን ጨረሼ መርማሪና ተመርማሪ ተለያየን። ከዛም ለአንድ ወር ማእከላዊ፣ከዛም ታጠቅ በመጨረሻም ዝዋይ ታስሬ በትምህርት ቤት ጉዋደኞቼ ብርታት ተፈትቼ ወደትምህርት ገበታ ተመለስኩ። ከወራት በሁዋላ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን በሰበር ዜና የአንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በሰው እጅ የመገደልን ዜና አወጁ። ቴሌቪዥኑ ሟች የተባለውን ባለስልጣን ፎቶ መግለጫ ከሚመስል ነገር ጋር እፊቴ ደቀነው፣ ይህ ሰው የደህንነት ሚኒስተሩ ሟች ክንፈ ገብረመድህን እንደሆነ ሲገልጽ፣ ማእከላዊ ምርመራ ላይ ያገኘሁት መርማሪ ለመሆኑ ምንም አልተጠራጠርኩም፣ እራሱ ነው።ወዲያውም በማእከላዊ ምርመራ የሰጠሁት ቃልና የተናገረው ነገር አእምሮየ ላይ አንቃጨለ።

ይህ አይነቱ ስድብ በአንድ ሰው ላይ ብቻ የደረሰ ሳይሆን፣በሌሎችንም የወያኔ ታሳሪዎች ላይ ተደጋግሞ ተከስቶአል። እዚህ ጋር ከሁለት ዓመት በፊት የሆነውን ማስታወሱ አግባብነት አለው፣ በወቅቱ መፈንቅለ መንግስት ሞክራችኋል በመባል ከተከሰሱት ዜጎች ውስጥ ብርጋዴል ጀነራል አሳምነው ጽጌ በእሰር ቤት የደረሰባቸው ድብደባ፣ ስድብና ማንቋሸሽ ለ'ነጻ'ው ፍርድ ቤት መናገራቸው የሚታወስ ነው። ጀኔራሉ በድብደባ የጠፋ አይናቸውንና የቆሰለ አካላቸውን በማሳየት ከሁሉም በላይ ግን የባሰባቸው “አማራ ሽንታም መሆኑን አታውቅም” እና ሌሎች ክብራቸውን የሚያንቋንሽሹ ስድቦች መሆናቸውን ለፍርድ ቤት ተብየው አስረድተዋል። ጀነራል አሳምነው በንግግራቸው አጉልተው የተናገሩት ይህን ስድብ ይሁን እንጂ ድብደባ የፈጸሙባቸው የወያኔ ደህንነት አባላት ከዚህም የዘለለ ነገሮችን ይናገሩ እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል። አንዱዓለም አራጌ፣ናትናኤል መኮንንና እስክድር ነጋ የዚህ አይነት ስድብና እንግልት እንደደረሰባቸው በቅርቡ ለፍርድ ቤት አቤት ማለታቸው የሚታወስ ነው።

መደምደሚያ፡

ውድ አንባቢያን ይህ ሁሉ ትረካ ውስጥ እንድገባ ያደረገኝ ከሰሞኑ፣ በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ጉራፋርዳ በተባለ ወረዳ የሚኖሩ ወደ 78 ሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናችሁ በሚል እስከ የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላልፎባቸው በሃይል መፈናቀል መጀመራቸውን በዜና መዘገቡ በመስማቱና ይሄ ነገር በእንጭጩ ካልተቀጨ መድረሻው የት እንደሆነ ለመጠቆም፣ የነገሩን ስረ መሰረት ግልጽ ለማድረግ ነው። ያም ብቻ ሳይሆን ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር እገሌ “የትግሬ ጥላቻ አለበት”  “የትግራይ ህዝብን ይጠላል” እያሉ በማሸማቀቅ፣ ነገር ግን በነሱ ውስጥ ያለውን የማይደበቅ የመረረ የህዝብ ጥላቻና በቀለኝነት ለማሳየት ነው። ምክንያቱም ለፖለቲካ ትክክለኝነት (Political Correctness) ወይንም በይሉኝታ ተሸብበን ያየነውንና የሰማነውን እንዳልሰማን ሆነን ነገሩን አለሳልሶ ለማለፍ የምናደርገው ጥረት፣ በወያኔዎች ዘንድ የሚሰጠው ትርጉም ፈሪነት ብቻ ነው። እዚህ ላይ ከወያኔ ባልተናነሰ መንገድ አንድም ለግዜያዊ ጥቅማቸውና ከዝናቸው በላይ አሻግረው ማየት የተሳናቸው የአማራ ልሂቃንን ጥፋት አሳንሶ ማለፉ ፍትህ ማጓደል ይሆናል። የችግሩ ቁልፍ ያለው ጠንካራ ድርጅትና ጠንካራ አመራር መስጠት የሚችል ሃይል መፍጠር አለመቻሉ ላይ ነውና፤ እንደ አማራ ሞቶ እንደ ኢትዮጵያዊ መወለጃውን ግዜ ማሰብ አሁን ነው።

ዋቢዎች

http://ebookbrowse.com/tplf-manifesto-1968-e-c-pdf-d237509169
http://addisvoice.com/2011/06/paul-henzes-coversations-with-meles-zenawi
http://addisnegeronline.com/2010/05/
http://ethio-wolqait.blogspot.com/2008/05/blog-post.html
http://ebookbrowse.com/tplf-cirime-against-humanity-and-genocide-committed-in-wollo-and-gonder-pdfd237509170
http://www.afrik-news.com/article15739.html
Ethiopia-Amhara census: A question of politics, money and manipulation?
http://www.aigaforum.com/2007 Ethiopoian_Census.pdf
The 2007 Population Census in the Amhara Region Is Underreported
http://blog.ethiopianmuslims.net/negashi/?p=284
Absurd Statistical Gimmick in Ethiopias 2007 Census By Cens Kerk
http://www.docstoc.com/docs/53962882/Absurd-statistical-gimmick-in-Ethiopias-2007-census-and-the
Absurd statistical gimmick in Ethiopia’s 2007 census and the need for accounting for the missing 3.0
million people in Amhara and Addis Ababa
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/5390-2012-02-29-06-25-08.html
በጉራፋርዳ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች አካባቢውን ልቀቁ መባላቸውን ገለጹ(WEDN, 29 FEB 2012)
http://www.ethiopianreporter.com/
ከምሥራቅ ወለጋ ወደቡሬ የተፈናቀሉት አማራዎች ቁጥር ከ12.000 በልጧል (ከሪፖርተር ጥር 28 ቀን 1993)
http://cyberethiopia.com/warka4/viewtopic.php?t=35623&sid=314401f4d0ee78a68831c379b4e30d4b
በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን በሜኒት ጎልዲያና በሜኒት ሻሻ ወረዳዎች በሕገወጥ መንገድ ሰፍረዋል የተባሉና ከአማራ ክልል የመጡ 3
56 አባወራዎች (804 ቤተሰቦች) ሰሞኑን ወደክልላቸው መመለሳቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገለፁ፡፡ (Wed Sep 02, 2009)
http://www.ethiopianreview.com/amharic/?p=4829
ቱኒዚያውያን ተገላገሉ፤ ግብፆችም …እኛስ
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/5827-2012-03-31-11-23-30.html
የጉራፋርዳ ተፈናቃዮች ወደ ደብረ ብርሃን ተጓጓዙ
http://www.ehrco.org/images/pdf/UrgentAppeal.pdf
URGENT APPEAL Protect the Rights of Displaced Citizens!

No comments:

Post a Comment