Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, April 8, 2012

ከብሔር ግጭቶች በስተጀርባ ማን አለ?

በ ኃይለመስቀል በሸዋምየለህ, (Fetehe.com)

በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለዞኑ አስተዳደር በፃፉት ደብዳቤ ነዋሪዎቹ ዞኑን ለቀው እንዲወጡ መገደዳቸው ያለፉት ሁለት ሳምንታት ቀዳሚ የአደባባይ አጀንዳ ነበር፡፡ ኢህአዴግ በጉዳዩ ላይ ምንም መናገር ባይፈቅድም የዜጐቹ መፈናቀል በኢትዮጵያ ውስጥ ተዘዋውሮ የመኖርን እና ንብረት የማፍራትን ህገ-መንግስታዊ መብቶች ስለመጣሱ የተለያዩ ተቋማት ሲሟገቱ ሰንብተዋል፡፡ ክስተቱ ለተፈናቃዮቹ መጠለያ በመስጠት የተባበረው መኢአድ ‹‹የተሳሳተ የመንግስት ፖሊሲ ውጤት›› እንደሆነ ሲናገር፤ መድረክ በበኩሉ ‹‹የህጋዊ ስርዓት መናጋት›› አድርጎ ቆጥሮታል፡፡ የእነዚህ ተፈናቃዮች መነሾ ሀገሪቱ ከተከተለችው የፌደራሊዝም ተገብሮት ጋር ይተሳሰራል፡፡ ክልሎች የራሳቸው ህገ-መንግስቶች እንዲኖራቸው ሲፈቀድ በየክልሉ የሚገኙት ነዋሪዎች ፖለቲካዊ ውክልናን በተመለከተ በሁለት ጠርዝ ላይ ይቆማሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ የክልሉ ነዋሪዎች በኢህአዴግ አጠራር ‹‹ሀገር በቀል›› የሚባሉት ሲሆኑ እኒህ ብሔሮች ‹‹ባለስልጣን›› Titular/ ተደርገው ሲቀርቡ፤ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ አነጋገር ‹‹ህገ-ወጥ ሰፋሪዎች›› የሚባሉት ‹‹ስልጣን-አልባ›› /Non-titular/ ቡድኖች ይሆናሉ፡፡የመጀመሪያዎቹ ክልላቸውን የማስተዳደርም ሆነ በየክልሎቻቸው ህገ-መንግስቶች የተቀመጡ መብቶችን ሲጎናፀፉ፤ ሌሎቹ ይህ የመብት እድልም ሆነ የፖለቲካ ውክልና ይነፈጋቸዋል፡፡ ከቤንጅ ማጂ ዞን የተባረሩት ዜጐችም በዚህ የ‹‹ስልጣን አልባነት›› ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ ለዘውግ ፌዴራሊዝም መሳለጥ ወሳኝ እንደሆነ የሚጠቀሰው  የብሄሮች አሰፋፈር ገፅታ ነው፡፡ በሀገሪቷ ውስጥ የሚገኙ የትኞቹም ብሄሮች አንድ የተወሰነ መልክዕ- ምድራዊ የአሰፋፈር ዘዬ ካላቸው የፌዴራሊዝሙን ሙከራ ያቀለዋል፡፡

ከዚህ በተፃራሪ ከአንድ የበለጡ ብሄሮችን በአንድ ክልል ውስጥ ለማቀፍ ሲሞከር ከላይ የተጠቀሰው ፖለቲካዊ ስልጣን ተኮር ክፍፍል ይከሰታል፡፡ ይኼ ሁነትም መፈናቀልን ጨምሮ ተደጋግመው ለሚከሰቱ የብሄር ግጭቶች ያጋልጣል፡ ፡ ከሳምንታት በፊት የተከሰተው የዜጐች መፈናቀል ለሃያ ዓመታት የተሞከረውን የብሄር ፖለቲካን እና ተያያዥ ሁነቶቹን ወደ አደባባይ ውይይት እንዲመጡ የሚያስገድድ ይመስላል፡፡ የብሄሮችን ነፃነት ማወጅ አልፎም ብሄር ተኮር ግጭቶችን ለመፍታት ብቸኛው መንገድ ነው የተባለው የዘውግ ፌዴራሊም ራሱን በራሱ እየበላ እንደሆነ የሚናገሩ የጉዳዩ ታዛቢዎች ባለፉት ሃያ ዓመታት የተከሰቱትን ብሄር ተኮር ግጭቶች ከብሄር ፖለቲካው አንፃር አዛምዶ ለማየት መሞከር ጉዳዩን የተሻለ ለመረዳት እንደሚጠቅም ያነሳሉ፡፡ ብሔርተኝነት ለምን? ህወሓት መሩ ኢህአዴግ የብሔር ፖለቲካን የሀገሪቱን ብቸኛ የፖለቲካ ተዋስኦ ከማድረግ በዘለለ የመንግስት አወቃቀሩን ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አላቆ በብሔር ለማዋቀር መወሰኑን በተመለከተ የሚቀርቡ መከራከሪያዎች ሁለት ተለዋጮችን አስተሳስረው የያዙ ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ከፓርቲው የትጥግ ትግል መነሾ ጋር ይያያዛል፡፡ ህወሓት የትጥቅ ትግሉን ሲጀመር ‹‹የአማራ›› የበላይነትን መግታት ቀዳሚ አላማው ነበር፡፡ ከዘመናዊት ኢትዮጵያ ነገስታት ጀምሮ እስከ ደርግ ድረስ ያለው ገዢ መደብ ‹‹የአማራን የበላይነት›› ለማስጠበቅ የቆመ ፖለቲካ አመራረጥ አንዱ መነሻ ነው፡፡ በዚህ መነሾ የተጀመረው ትግል የደርግን ውድቀት ሲያቃርብ ራሱን ወደ ህብረ-ብሄራዊነት ማሻገር ያልቻለው ህወሓት፤ ትግራይ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም ብሔሮች በአን ‹‹ተጨቁነዋል›› የሚባሉትን ብሄሮች ለማሰባሰብ መፈለጉ ለብሄር ፖለቲካው መጠንከር የመጀመሪያ ምክንያት እንደሆነ ፕ/ር አብዲ ሳማተር “Ethiopia’s election: a bombshell or turning point?” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ሁለተኛው  መከራከሪያ ፓርቲው ከሚፈልገው ፍፁም የስልጣን የበላይነት ይነሳል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ የፃፉት ፕ/ር መሳይ ከበደ ይህ የብሄር ፖለቲካ ፓርቲውን እንዴት በስልጣን ላይ ሊያቆየው እንደሚችል ይተነትናሉ፡ ፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን የሚመለከታት የ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦች›› ድምር ውጤት አድርጎ ነው፡፡ የብሔር ቅራኔ በቀዳሚነት መፈታት አለበት፤ መከበርም ያለበት የብሄር መብት ነው የሚለው የፓርቲው ሙግት ሌሎች ተገዳዳሪ የፖለቲካ ልሂቃንንም በክሏል፡፡ ይህም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዋነኛ የመፎካከሪያ ቦታቸውን በፌደራል መንግስቱ ላይ ከማድረግ ይልቅ በክልሎች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ሁኔታዎቹ ማስገደዳቸው የተጠቀሰውን የገዢውን ፓርቲ የስልጣን ጠቅላይነት ህልም ለመተግበር እንደሆነ ፕ/ር መሳይ “The TPLF and the strategy of hejemony through federalism” በሚለው ፅሁፋቸው ይከራከራሉ፡፡

አንዳንድ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም አጥኚዎች የዘውግን የማህበራዊ ተለጣጭነት ባህሪይ በመጥቀስ ፌደራሊዝሙ ይህን ሊያካትት ባለመሞከሩ የ‹‹ኮንቲነር ፌዴራሊዝም›› ብለው እንዲጠሩት አስገድዷል፡፡ ፕ/ር ጆን አቢቢኒክ ቋንቋን መሰረት በማድረግ የተዋቀሩት ክልሎች ወጥ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መገለጫ እንደሌላቸው በመጥቀስ አሁን ካለው አወቃቀር ይልቅ ወለጋ ከጉምዝ፣ ጎጃም ከወለጋ አልያም አፋር ከትግራይ ቢካለል የተሻለ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን በ‹‹ኮንቲነሩ ፌዴራሊዝም›› ይህን ለማድረግ ኢህአዴግ ቢያንስ የዘውግ ፖለቲካውን ሊያለዝበው እንደሚገባም ያምናሉ፡፡ ፓርቲው በበኩሉ ባለፉት መንግስታት የተሞከረው የአሀዳዊ መንግስት ውድቀት ይህን
የቋንቋ ተኮሩን ፌዴራሊዝም አማራጭ አድርገው እንዲሞክሩት እንዳስገደዳቸው ይከራከራሉ፡፡

 ፕ/ር ክርስቶፈር ክላፍም “Nationalism, Nationality and regionalism” በሚለው ፅሁፋቸው አቶ መለስ ፌዴራሊዝሙ የተሻለ የፖለቲካ ስርዓት ስለማምጣቱ ተጠይቀው ‹‹በፍፁም አላውቅም፡፡ የማውቀው ሀገሪቱ እንዳትበታተን ይህ የመጨረሻ ሙከራችን መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ሂደት ሀገሪቱ የምትፈርስ ከሆነ መጀመሪያውኑ አልነበረችም ማለት ነው›› ማለታቸውን ያስነብባሉ፡፡ እርሳቸው ያለፉት ስርዓታት የብሄር ማንነትን ለመቀበል በመቸገራቸው ቢወቅሷቸውም፤ ፓርቲያቸው ያነበረው ፌዴራሊዝም ከዘውግ ማንነት ውጪ ያሉ ማህበረሰባዊም ሆነ ግላዊ መለዮዎች እንዳሉ ለመቀበል መቸገሩ ከወደቁት የፖለቲካ ስርዓቶች ጋር ያመሳስለዋል፡፡ የህወሓት እጅ? ባለፉት ሃያ ዓመታት ከተፈጠሩት ብሔር-ተኮር ግጭቶች መሀከል የህወሓትን ተፅዕኖ እና የግጭት አፈታት ክስረት በበለጠ ያሳያል በሚል በፀሐፊዎች የሚጠቀሰው ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በጋምቤላ የተከሰተው ተመላላሽ የብሄሮች ግጭት ነው፡፡ ኢህአዴግ ከተገበረው የብሄር ፌዴራሊዝም አንፃር እንደ አማርኛ፣ ትግሪኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሉት የየራሳቸው ክልል እንዲኖራቸው ከተደረገ ቢያንስ እኛም ዋነኛ ተወካዮች የሆንበት የፖለቲካ ስርዓት በክልሉ ውስጥ መስፈን አለበት የሚለው የአኝዋክ ልሂቃን ፖለቲካዊ መግፍኤ እንደሆነ ብዙ የክልሉ አጥኚዎች ይስማማሉ፡፡ ዶ/ር ጆን ያንግ “Along Ethiopia’s western frontiers: Gambella and Benishangul in transition” በሚለው ስራቸው እንደሚያነሱት ኢህአዴግ ህገ- መንግስቱ እንደሚያዘው በክልሉ ለሚገኙት ብሔሮች ክልል እንዲያቋቁሙ ከመፍቀድ ይልቅ ለብሔሮቹ የ‹‹ተመጣጣኝ ውክልና›› አካሄድን መምረጡ ከአኝዋኮቹ ልሂቃን ጋር እንዳጋጨው ይናገራሉ፡፡

 በ1984 ዓ.ም. ከ200 በላይ የሚሆኑ የአማርኛ እና የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መገደላቸውን የሚናገሩት ኤድዋንድ ኩሪሞቶ የተባሉ ፀሐፊ ለዚህ ጥቃት ሌሎቹ ተጎጂዎች በሌሎቹ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ የበቀል ጥቃት መፈፀማቸውን በማንሳት፣ የግጭቱ ሁሉ መነሻ ህወሓት በትጥቅ ት ግሉ መዳረሻ ዓመታት እና ከዛ በተከተሉት ጊዜያት ከአኝዋክ ብሔር ልሂቃን ጋር የገባበት የፖለቲካ ንትርክ እንደሆነ “Politicization of ethnicity in Gambela” በሚለው ፅሁፋቸው ይናገራሉ፡፡ በ1987 ዓ.ም. በፀደቀው ህገ-መንግስት መሰረት የስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ የተነገረው ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች›› ሲሆኑ ከዚህ መንፈስ ጋር በተዛመደ ክልሎች የራሳቸውን ህገ- መንግስት እንዲቀርፁ በመፈቀዱ በጋምቤላ ክልል -መንግስት መሰረት የስልጣን ባለቤቶች እንዲሆኑ የተወሰነው በክልሉ ያሉ አምስት በህወሓት አጠራር ‹‹ሀገር-በቀል›› ብሔሮች ናቸው፡፡ በዚህ የዘውግ ፖለቲካ ትርጓሜ መሰረት በክልሉ የሚገኙ የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች በክልሉ የፖለቲካ ተቋማት ውስጥ ውክልና አይኖራቸውም፡፡ እነዚህ በዋናነት የሶስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ትግሪኛና ኦሮምኛ) ተናጋሪ የሆኑ ዜጐች ለክልሉ እስከ 50% የሚሆን የተማረ የሰራተኛ ሃይል ከማዋጣት በዘለለ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ሚና ቢኖራቸውም ከቋንቋ-ተኮሩ የፌደራሊዝም ስርዓት አንፃር በክልሉ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ እድል ተነፍገዋል፡፡

 የክልሉን የፖለቲካ ጠመዝማዛነት ያጠኑ ፀሐፊዎች እንደሚያነሱት በክልሉ የተፈጠሩት የብሔር ግጭቶች በኢህአዴግ እና በአኝዋክ ልሂቃን ከተገበረው የፀረ-ደርግ ትብብር ላይ ይነሳል፡፡ በቅድመ-ደርግ ዘመን በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ታጣቂ ቡድኖች ውስጥ አንዱ የነበረው የጋምቤላ ህዝብ ነፃ  አውጪ ንቅናቄ /ጋህነን/ ከኢህአዴግ ጋር የጋራ ፀረ- ደርግ ትግል ለማድረግ ሲስማማ ኢህአዴግ የክልሉን ስልጣን እንደሚሰጠው ተስማምቶ እንደነበር ዶ/ር ደረጄ ፈይሳ ይጠቅሳሉ፡፡ የኑዌርን ብሔር የደርግ አጋዥ ሀይል አድርጎ ያሰበው ኢህአዴግ ከአኝዋኩ ፓርቲ ጋራ የመተባበር መንፈስ ቢያሳይም ከሽግግሩ መንግስት ምስረታ ማግስት የኢህአዴግን የብቻ የስልጣን ጠቅላይነት የተገዳደረው ጋህነን የመፍረስ አደጋ ተጋረጠበት፡፡ ዶ/ር ደረጄ እንደሚሉት ኢህአዴግ ፓርቲውን በማፍረስ ለስርዓቱ ታማኝ በሆነ የአኝዋክ ልሂቃን እንዲመራ አደረገው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሌላው የኑዌር ፓርቲ ጋር በማዳቀል ዶ/ሩ ‹‹ከንቱ›› (Docile) ሲሉ የጠሩትን የጋምቤላ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን /ጋህዲግ/ መሰረተ፡፡ በዚህ የገዢው ፓርቲ አካሄድ እና እስከጊዜው ድረስ በጠላትነት ያያቸው የነበሩትን የኑዌር ልሂቃን ወደ ክልሉ ስልጣን ለማቅረብ መሞከሩ በአኝዋኮች በኩል የ‹‹ተገፍተናል›› ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡

ለኢትዮ- ኤርትራው ጦርነት ከሌሎቹ ብሔሮች የተሻለ አስተዋፅኦ አድርጋችኋል በሚል ሰበብ የኑዌር ተወላጅ ፖለቲከኞችን በተሻለ ሁኔታ አብልጦ ወደ ስልጣን ለማቅረብ የተደረገው ሙከራ በሁለ  ብሄሮች መሀከል ከፍተኛ ትንቅንቅን ፈጠረ፡፡ ፕ/ር ጆን አቢቢኒክ እንደሚሉት ይህን የገዢውን ፓርቲ የፖለቲካ ውሳኔ አስመልክቶ በሁለቱ ብሔር ልሂቃን መሀከል የተቀሰቀሰው መፈራቀቅ ለብዙ ዜጎች ሞት ምክንያት ሆነ፡፡ ይህን ህወሓት አነሳስቶታል ተብሎ የሚጠቀሰውን የሁለቱን ብሔሮች ግጭት ለማብረድ በሚል የአኝዋክ ብሔር ተወላጅ የነበሩት የክልሉ ፕሬዝዳንት ሲታሰሩ፣ ሌሎች ፓርቲው በተሳታፊነት ከከሰሷቸው የክልሉ የፖሊስ አባላት መሀከል ብዙዎቹ ከስራቸው ተባረሩ፡፡ ዶ/ር ደረጄ “A national perspective on the conflict in Gambela” በሚል ርዕስ ለ16ኛው የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ ባቀረቡት ጥናት እንደሚከራከሩት ኢህአዴግ ለክልሉ አለመረጋጋት መንስኤ የፓርቲዎቹ መብዛት ነው ከሚል መነሻ ሁሉንም ፓርቲዎች ጨፍልቆ አዲስ ‹‹የጋምቤላ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ›› የሚል ሳተላይት ፓርቲ አደራጀ፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት የተቆጡት የአኝዋክ ልሂቃን አመፅን አማራጫቸው አደረጉ፡፡

አመፃቸው ገዢው ፓርቲ ላይ ብቻ ከመሆኑ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙትን የሌሎች ብሄሮችን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ በ1994 ዓ.ም. ለተፈጠረው የብሔሮቹ ግጭቶች መነሻ እንደሆነ ፕ/ር አቢቢኒክ “Ethnic based federalism and ethnicity in Ethiopia: reassessing the experiment after 20 years.” በሚለው ጥናታቸው ያወሳሉ፡፡ ፀሐፊዎቹ እንደሚናገሩት የፌዴራል ፖሊስ በተሳተፈበት በዚህ ግጭት እስከ 400 የሚደርሱ የአኝዋክ ተወላጆች ተገድለዋል፡፡ ከዚህ ደም አፋሳሽ ግጭት በኋላ ወደ ሱዳን የሸሹት የአኝዋክ ብሄር ተወላጆች የጋምቤላ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባርን በመመስረት በማዕከላዊ መንግስቱ ላይ ወታደራዊ ጥቃቶችን እስከመፈፀም ደረሱ፡፡ ዶ/ር ደረጀ በበኩላቸው ለኢህአዴግ እና ለአኝዋኮች ግጭት መባባስ በማሌዢያው ፔትሮናስ የነዳጅ ኩባንያ አማካኝነት እየተፈለገ ያለው ነዳጅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይተነትናሉ፡፡ የሀገሪቱን ህገ-መንግስት እና የገዢውን ፓርቲ ፖለቲካዊ ተግብሮት አያይዘው ያጠኑ ምሁራን እንደሚሉት በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ከክልሉ የፖለቲካ ስርዓት መገለላቸው የህገ-መንግስቱን ዕሴቶች መፃረር ነው፡፡ ከነዚህ መሰል ተከራካሪዎች አንዱ የሆኑት አሰፋ ፍሰሃ “Federalism and the adjudication of constitutional issues” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው እንደሚሉት አንድ የሌላ ብሄር ተወላጅ በሌላ ክልል ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልገው የክልሉን  የስራ ቋንቋ ማወቅ ብቻ ነው፡፡

በዚህ ክርክር በጋምቤላም ሆነ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች የክልሉን የስራ ቋንቋ እስካወቁ ድረስ በክልሉ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ አለመወከላቸው እጅግ ፀረ ህገ-መንግስታዊ አካሄድ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ገዢው ፓርቲ ያለውን ተፃራሪ አቋም የምንመለከተው በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል መሀከል ያለውን ንፅፅር ስንመለከት ነው፡፡ እንደጋምቤላ ሁሉ በቤኒሻንጉል-ጉምዝ ክልል ውስጥ ብዙ የሌሎች ብሔር አባላት ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን በክልሉ ያሉት ዜጐች ውክልና ይገባናል ብለው ስርዓቱን ለማስገደድ መሞከራቸው በክልሉ ውስጥ መምረጥም ሆነ መመረጥ እንደሚችሉ የፌዴሬሽን  ምክር ቤት ወስኗል፡፡ የኢህአዴግን የዘውግ ፖለቲካ አተገባበር ኃልዮታዊ በሆነ መንገድ ለመተንተን አስቸጋሪ የሚያደርገው ይህን መሰሉ ባለሁለት መስፈርት የፓርቲው አካሄድ እንደሆነ የጉዳዩ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ በቤኒሻንጉል-ጉምዝ ክልል ውስጥ ሚገኙት ብሔሮች መካከል ስለተፈጠሩት ግጭቶች ያጠኑት ፕ/ር አቢቢኒክ እንደጋምቤላው ሁነት ሁሉ በዚህ ክልልም የተፈጠሩት ግጭቶች ዋነኛ መነሻ የክልሉን የፖለቲካ ስልጣን የሚንተራስ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

 እንደ አጥኚው በጉምዝ እና በበርታ እንዲሁም በበርታ እና በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪው መሀከል የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ ለአማረኛ ቋንቋ ተናጋሪው ክፍል ‹‹ልዩ ወረዳ›› በመሰየም ግጭቱን ለማብረድ የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ጥረት አድርጓል፡፡ ፌደራሊዝሙ እንደሚፈቅደው በሚገባ አልተወከልንም ያሉ የየብሔሩ ልሂቃን እየተመላለሱ ክልሉን በሚንጥ የብሔር ግጭት ውስጥ እንዲያል በገዢው ፓርቲ የብሔር ፖለቲካ ተዋስኦ መገደዳቸውን ፕ/ሩ ከላይ በተጠቀሰው ፅሁፋቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹የድንበር ብሔርተኝነት›› በሀገሪቱ ውስጥ ተደጋግመው ለተከሰቱት የብሄር ግጭቶች ሌላኛው መነሻ በብሔሮች መሀከል የሚፈጠረው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ነው፡፡ ቋንቋ ተኮሩን ፌዴራሊዝም የሚተቹ ጸሐፊዎች ደጋግመው ያነሱ ከነበረው ጥያቄ አንዱ አንድን የቋንቋ ተናጋሪ በአንድ ወጥ ድንበር ውስጥ መከለል አይቻልም፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ትስስሮሽ ለዚህ መሰሉ አከላለል አይመችም የሚል ነበር፡፡ ምፀታዊ በሆነ መንገድ ገዢው ፓርቲ ገፍቶ የሄደበትን የፌደራሊዝም አወቃቀር ተከትሎ ለተነሱት የብሄር ግጭቶች አንደኛው መነሻ ምሁራን ‹‹የድንበር ብሄርተኝነት›› (Ethnicisation of territory) ሲሉ የሰየሙት ሁነት ነው፡፡ በጌድዮ እና በጉጂ ኦሮሞዎች መሀከል መብረድ ያልቻለው ግጭት በዚህ ‹‹የድንበር ብሄርተኝነት›› ሙግት የሚብራራ ነው፡፡

እስከ 1983 ዓ.ም. በሲዳማ ክልል ውስጥ ተካተው ይኖሩ የነበሩት እኒህ ‹‹ብሔረሰቦች›› የፌደራሊዝሙን አዲስ የክልል አወቃቀር ተከትሎ ጉጂ ወደ ኦሮሚያ፣ ጌዲዮ ወደ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል እንዲጠቃለሉ ተወሰነ፡፡ በአንድ ላይ እንደኖሩ ብሔሮች መንደሮችን በጋራ እስከመመስረት በደረሱት እነዚህ ብሔሮች መሀከል ድንበር ለመለየት የተደረገው ሙከራ ግጭቶችን እንዲወልድ ግድ ብሏል፡፡ አሰበ ረጋሳ የተባሉ ፀሐፊ እንደሚሉት በሁለቱ መሀከል ያለውን ቅሬታ እንዲያባብስ ያደረገው አንዱ ምክንያት የጉጂ ብሔር አባላት በደም የሚዛመዷቸው ሰዎች ወደ ጌዲዮ መጠቃለላቸው ነው፡፡ በሁለቱ መሀከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የፌዴራል መንግስቱ የድንበሩን ጥያቄ በሪፈረንደም ለመፍታት ቢሞክርም፤ ሪፈረንደሙ ውጤት ሊያመጣ ስላልቻለ ግጭቶቹ ሊረግቡ አልቻሉም፡፡ አሰበ ረጋሳ ‹‹Ethnicity and Inter-ethnic relation in the “Ethiopian experiment’ and the case of the Guji and Gadeo›› በሚለው ፅሁፋቸው እንደሚጠቅሱት ድንበርን ማዕከል አድርጎ በተቀሰቀሰው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች አልቀዋል፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ “Ethnicity and political parties in Africa: The case of ethnic based parties in Ethiopia” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው ይህን መስሉ በሁለቱ ብሔሮች መሀከል የተፈጠረው ግጭት መሰረታዊ መፍትሄ ለማግኘት ስለመቻሉ እርግጠኛ አለመሆናቸውን ያስነብባሉ፡፡

 “The Silte model” የብሔር ፖለቲካው ከብሔሮች ግጭት በተጨማሪ አመጣቸው  ሚባሉት አደገኛ ክስተቶች አንደኛው የነገሩ ተከታዮች ‹‹የዘውግ ስራ- ፈጣሪዎች›› /Ethnic entrepreneurs/ በሚባሉት ጥቅመኛ ልሂቃን የሚቀሰቀሰው ‹‹የራሳችን ዞን ይሰጠን›› አልያም ‹‹ማንነታችን ታውቆ የራሳችን ክልል ይፈቀድልን›› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ የሀገሪቱ የፖለቲካ ተከታታዮች ይህንን እየዳበረ ያለ ብሄርተኛ አካሄድ ‹‹የስልጤ ሞዴል›› ሲሉ ይጠሩታል፡፡ እስከ ጥቂት ዓመታት ድረስ ጉራጌ በሚባለው ብሔር ስያሜ የሚታወቀው የስልጤ ብሄር፤ ገዢው ፓርቲ ካስተዋወቀው ጥንተ-ነገር /Primordial/ ማንነቶች ላይ ከሚነሳው የብሄር ፖለቲካ አስተምህሮት በመነሳት ‹‹ጉራጌ አይደለንም›› የሚል ጥያቄ በብሄሩ ልሂቃን በኩል ተነሳ ፕ/ር ጆን ማርካሊስ እንደሚሉት ለስልጤ ጥቅመኛ ልሂቃን አነሳስ ይህ የፓርቲው የብሄር ፖለቲካ አረዳድ በጉራጌኛ ተናጋሪው እና በስልጤ መሀከል የማንነት ልዩነት ወጥቶ እንዲግለበለብ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

 በጥያቄው ላይ የተደረገውን ሪፈረንደም የተከታተሉት ዶ/ር ላራ ስሚዝ እንደ ሬድዋን ሁሴን እና መሰሎቹ የብሄሩ ልሂቃን እስልምናን፣ ቋንቋን እና ኢኮኖሚያዊ መገፋትን የመሰሉ ተለዋዋጭ አጀንዳዎችን በመጠቀም ጥያቄውን የድጋፍ መሰረት እንዲይዝ ታትረዋል ሲሉ ይከሷቸዋል፡፡ የዞን ጥያቄው በሪፈረንደም መመለስ ዞኑን እንዲያስተዳድሩ ዕድል ስለሚሰጣቸው፤ ይኽም የልሂቃኑ የማንነት ጥያቄ መግፍኤ መሆኑን ዶ/ሯ ያወሳሉ፡፡ ሌሎች በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ህዳጣን ብሄሮች ይህን መሰል ጥያቄ እንዳያነሱ የ ሚያ ርጋቸው አስገዳጅ ምክንያት ብዙ የለም፡፡ ነገሩን እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው በአዲስ ዞን አከላለል ወቅት የሚነሱ የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የፌደራል መንግስቱ ከአጠቃላይ የአስተዳደር ሸክሞችና ተያያዥ ወጪዎች አንፃር ሌሎች ይህን መሰል ‹‹የማንነት ጥያቄዎችን›› ለማስተናገድ ሲቸገር ቢስተዋልም ሂደቱን ለመግታት የሚቻለው አይመስልም፡፡

ባህላዊ ማንነታቸው የተለንቀጠ ብሔሮች መሀከል ይህ ‹‹የስልጤ ሞዴል›› ሊተገበር ከተሞከረ በብሔሮቹ መሀከል የተለያዩ ጭብጦችን ማዕከል ያደረጉ ግጭቶች ሊቀሰቀሱ ይችላሉ የሚለው የብዙዎቹ የፖለቲካው ተከታታዮች ስጋት ነው፡፡ የስልጤ የማንነት ጥያቄ ምላሽን ወደ ፌደራሉ የስልጣን ጥግ መወጣጫ ያደረጉ ልሂቃን መኖራቸው ሌሎች አቻ ብሔርተኛ ፖለቲከኞችን ወደዚህ የዘውግ ኢንተርፕርነርነት ይስባል የሚለው ሌላው የስጋት ጫፍ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment