Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, April 8, 2012

የኦሮሚያ ክልል ለስኳር ልማት ፕሮጀክት የሚነሱ ነዋሪዎችን ለማስፈር እየተዘጋጀ ነው

 By Ethiopian reporter

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለአርጆ ዴዴሳ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከሚፈልገው ቦታ ላይ የሚነሱ ነዋሪዎችን ዳግም ለማስፈር ዝግጁቱን እያካሄደ ነው፡፡ የኦሮሚያ መሬትና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ የስኳር ልማቱ ከሚፈልገው ቦታ ላይ የሚነሱ ነዋሪዎችን በድጋሚ ለማስፈር የሚያስችለውን ሥራ፣ ከኢሉአባቦራና ከምሥራቅ ወለጋ ዞኖች ጋር በመነጋገር እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አቡዱልአዚዝ መሐመድ እንደገለጹት፣ በአፋጣኝ የሚነሱት ነዋሪዎች በአልሐበሻ ስኳር ፋብሪካ የማስፋፊያ ክልል ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ይህ እንደተጠናቀቀ የስኳር ልማት ኮርፖሬሽን ሊያለማ ካቀደው ቦታ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ይነሳሉ፡፡

በኢሉአባቦራ ዞንና በምሥራቅ ወለጋ ዞኖች መካከል ላይ በሚገኘው የዴዴሳ ሸለቆ 100 ሺሕ ሔክታር የሚጠጋ መሬት ለስኳር ልማት እንዲውል ታቅዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከዚህ ውስጥ 16 ሺሕ ሔክታር የሚሆነው በፓኪስታኑ ኩባንያ አልሐበሻ ስኳር ፋብሪካ በመልማት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀሪው 64 ሺሕ ሔክታር በኮርፖሬሽኑና በፓኪስታኑ ኩባንያ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የሚፈለግ ነው፡፡ የተቀረው 12 ሺሕ ሔክታር በዴዴሳ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ያለው የመስኖ ግድብ የሚፈጥረው ሐይቅ የሚያርፍበት ቦታ ነው ተብሏል፡፡

ከአጠቃላዩ ቦታ 138 ሺሕ ሰዎች ይነሳሉ ሲሉ ውስጥ አዋቂዎች ለሪፖርተር ቢገልጹም፣ አቶ አቡዱልአዚዝ ጥናቱ ተጠናቆ ያልቀረበላቸው በመሆኑ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ነገር ግን የሚነሱ ነዋሪዎች ተለዋጭ ቦታና ተመጣጣኝ ካሣ በሕጉ መሠረት እንደሚያገኙ አቶ አቡዱልአዚዝ አስረድተዋል፡፡ 
የግድቡን ግንባታ የኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በማካሄድ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ሥራም 1.6 ቢሊዮን ብር ተከፍሎታል፡፡ የመሬት አጠቃቀም ጥናቱን በ43 ሚሊዮን ብር፣ የግድብ ግንባታውን በ11 ሚሊዮን ብር የሚያካሂደው የኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ኩምሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሁሉም ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ ነው፡፡ በዴዴሳ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ በመንግሥት ለሚገነባው የስኳር ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን፣ ኩታ ገጠም በሆነ ቦታ ላይ ለተገነባው ለፓኪስታኑ አልሐበሻ ስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ እርሻም ውኃ እንደሚሰጥ አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡

የፓኪስታኑ ኩባንያ የስኳር ፋብሪካ በመጠናቀቅ ላይ ቢሆንም፣ ኩባንያው በገጠመው የፋይናንስ ችግር ምክንያት መንግሥት በሽርክና ወይም ሙሉ በሙሉ ፋብሪካውን ጠቅልሎ ሊወስደው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኮርፖሬሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይልማ ጥበቡ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አልሐበሻ ስኳር ፋብሪካ ወደ መንግሥት ይዞታነት ለማስገባት በጥናት ላይ ነው፡፡

መንግሥት ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ በአገሪቱ 11 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች የመገንባት ዕቅድ አለው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ይፈስባቸዋል ነው የሚባለው፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከ200 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ የሚፈልጉ ሲሆን፣ አጠቃላዩ የሥራ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በአቶ ዓባይ ፀሐዬ እየተመራ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment