‹‹አረብ ስፕሪንግ››ን ተከትሎ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፖለቲካ
ተንታኞች በዘርፈ ብዙ ቅሬታ በተሞላችው ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነገር መከሰቱ አይቀሬ እንደሆነ ደግመው ደጋግመው
መተንተናቸው ይታወሳል፡፡ ለድምዳሜያቸው ገፊ ምክንያት አድርገው ከወሰዷቸው ችግሮች ውስጥ ስርዓቱ ለሁለት አስርታት
በስልጣን ላይ መቆየቱ፣ አስከፊ ድህነት መስፈኑ፣ የስራ አጥ ቁጥር ማሻቀቡ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ክብር
አልባ መሆናቸው፣ የፍትህ እጦት… ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ቁጥራቸው የበዛ ምሁራኖች እነዚህ ችግሮች በጊዜ መፍትሄ ካላገኙ
አብዮት ወደ ሚያቀጣጥል ‹‹ካምሱር››ነት ለመቀየራቸው የተለያዩ ሀገራትን ታሪክ ጭምር ጠቅሰው በርካታ ፅሁፎችን
አስነብበዋል፡፡ የሆነ ሆኖ የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ
የተፈጠረውን መነቃቃት ለማደብዘዝ ስርዓቱ ራሱን ለተጋነነ ወጪ መዳረጉ ይነገራል፡፡ በተለይም የደህንነት ተቋሙን፣
መከላከያ እና የፖሊስ ሠራዊትን ለማጠናከር የሀገር ሃብት ባክኗል፡፡


