Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, March 31, 2013

ከቤንሻንጉል አማርኛ ተናጋሪ ዜጎችን በግፍ የማፈናቀሉ ተጠናክሮ ቀጥሏል

-ጥቃቱ ህፃናትና አረጋውያን ላይም እየደረሰ ነው
አማርኛ ተናጋሪውን ከየቦታው የማፈናቀሉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የመረጃ ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡ የፍኖተ ነፃነት ምንጮች እንደሚሉት በዚህ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይ ዞን ያሶ ወረዳ 25 ሺህ አማርኛ ተናጋሪዎች እየተደበደቡ በጭነት መኪና ተጭነው ከመኖሪያቸው ተባረዋል፡፡ የአካባቢው የዓይን ምስክሮችም ተጧሪ አረጋዊያንና ህፃናት “ውሃ፣ አምባሻ እያሉ በየመንገዱ ሲለምኑ ያለርህራሄ እየደበደቧቸው ወስደዋቸዋል፡፡” ሲሉ በቅሬታ ያስረዱሉ፡፡


ፍኖተ ነፃነት ያነጋገረቻቸው የዓይን ምስሮች እንደሚሉት መንታ የተገላገለች እመጫት ሳትቀር አስር ቀን ሳይሞላት በጭነት መኪና ላይ ወርውረዋት አከባቢውን ለቃ እንድትሄድ ተደርጓል፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ለመረዳት እንደቻለው አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ከ96 ዓ.ም ጀምሮ በባዶ መሬት ላይ ሠፍረው አካባቢውን ያለሙ የነበሩ ናቸው፡፡ የዘሩትን እህል ሳይሰበስቡና ንብረታቸውን ሳይዙ እየተባረሩ የሚገኙት እነዚህ የአማርኛ ተናጋሪ ዜጎች የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም እየደረሱባቸው እንደሚገኝ ፍኖተ ነፃነት ከአይን እማኞች ለማረጋገጥ ችላለች፡፡ 

ምንጮቻችን አክለውም “ሰው መሆን እስከሚያስጠላ ድረስ በጭካኔ እየደበደቡ መሬት ለመሬት እየጎተቱ መኪና ላይ ይወረውሯቸዋል፡፡ በአካባቢው ኦሮሚኛ እና ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች በተመሳሳይ ጊዜና ከዚያ ወዲህ በቅርብ ጊዜ ሠፍረው የሚኖሩ አሉ፡፡ እነሱን የሚነካቸውና የሚጠይቃቸው የለም፡፡” በማለት አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ያነጣጠረ ዘር የማፅዳት ዘመቻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ፍኖተ ነፃነት ያነጋገረቻቸው በአካባቢው በንግድ ስራ የተሰማሩ ግለሰብ እንደሚናገሩት አማርኛ ተናጋሪዎቹን ከስፍራው ለማፈናቀል ከሚሰጡት ምክንያት አንዱ “ከዚህ በፊት በክልላችሁ በነበራችሁበት ቦታ የማዳበሪያ ዕዳ አለባቸው” የሚል ነው፡፡ ግለሰቡ አክለውም “ዕዳ ካለባቸው ባሉበት በህግ መጠየቅ እየተቻለ ሁሉንም ወንጀለኞች ናቸው እየተባለ መደብደብና ማባረር ወንጀል ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አያይዘውም ብአዴን በአማራ ህዝብ ስም ሥልጣን ላይ ተቀምጦ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን እያየ እንዳላየ ዝም ብሎአል፡፡ አቤቱታ እየቀረበላቸው አንድም ነገር አላሉም፡፡ ብአዴን የአማራ ህዝብ ወኪል አለመሆኑን ሙሉ በሙሉ ያረጋገጠበት ወቅት ላይ ደርሷል፡፡” ሲሉ እጅግ አዝነው ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን እያስፈጸሙ ናቸው የተባሉትን የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ሻምበልን በስልክ አግኝተናቸው ነበር፡፡ እራሳችንን አስተዋውቀን ጥያቄያችንን ልንጀምር ስንል አቶ ታደሰ ስልካቸውን ጆሮአችን ላይ በመዝጋታቸው ዜናው ሚዛናዊ ለማድረግ አልቻልንም፡፡

በዚህ ሳምንት ከወረዳው ተባረው በመጓጓዝ ላይ የነበሩ ዜጎችን ጭኖ የነበረው አንዱ መኪና ተገልብጦ 59 ሰዎች ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡ ህይወታቸው ካለፈው ውስጥ አብዛኞቹ ህጻናት፣ሴቶችና አረጋውያን መሆናቸውን በስፍራው የተገኙ የዓይን ምስክሮች ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች:

No comments:

Post a Comment