Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, December 19, 2012

ሽጉጥ ያስመዘዘ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ

ከዳዊት
Gibi Gebriel Ethiopian Orthodox church
(አንድ አድርገን ታህሳስ 9 2005 ዓ.ም)፡- በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል  ገዳም (በተለምዶ ግቢ ገብርኤል) እየተባለ የሚጠራው የቤተክርስትያን ቅጥር ውስጥ  በምዕመናን እና በገዳሙ አመራሮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ድንጋይ መወርወሩንና የገዳሙ ገንዘብ ቤት ኃላፊ የሆኑት መምሬ ንጉሴ የታጠቁት ሽጉጥ መምዘዛቸውን በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ምዕመናኑንና የገዳሙን አመራር ለልዩነት የዳረገው ምክንያት የሰበካ ጉባኤ አባላት አመራረጥ ሂደት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደ መረጃ ምንጮቻችን በ2003 ዓ.ም ወርሃ መጋቢት በተደረገ ምርጫ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሰበካ ጉባኤ የገዳሙንና የሃይማኖቱን ቃለ አዋዲ በጠበቀ መልኩ ወደ ስራ ገብተው ነበር፡፡ ከአዲሱ ሰበካ ጉባኤ በፊት የነበሩት የሰበካ ጉባኤ አባላት የገዳሙን ገንዘብ በመመሳጠር ሲዘርፉ በመቆየታቸው የተነሳ የስራ ዘመናቸውን ሳያጠናቅቁ እንዲሰናበቱ ተደርገው ነበር፡፡

አዲሶቹ አባላት የገዳሙን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በጀመሩበት ወቅት የሚታይ ለውጥ መንገሱን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ ምንጮቻችን ማብራሪያ ሲያክሉም “ይህ ሰበካ ጉባኤ ከመመረጡ አስቀድሞ በወር ሁለት ጊዜ የገዳሙን የሙዳየ ምጽዋት ገቢ ይቆጠር ነበር፡፡ በዚያው ወቅት እስከ 18 ባሉት ቀናት በሚደረግ ቆጠራ ተገኝ የሚባለው ገንዘብ ከ70ሺህ ብር አይበልጥም ነበር፡፡ የቅዱስ ገብርኤል እለት ሲሆን ከፍተኛ ገቢ እንደሚገኝ መገመት የማያዳግት ቢሆንም ቆጣሪዎቹ ቢበዛ 140ሺህ ብር በላይ ተገኝ ብለው አያውቁም፡፡ ነገር ግን አዲሱ ሰበካ ጉባኤ እስከ 18 የሚያደርገው ቆጠራ 140ሺህ ብር ሲደርስ እንዲሁም በቅዱስ ገብርኤል ዕለት 230ሺህ ያህል መገኝቱን ይፋ ማድረግ ጀመረ፡፡ የቀድሞው እና የአሁኑ ሰበካ ጉባኤ ይመዘግቧቸው የነበሩ ገቢዎች በዳታ የተያዙ በመሆናቸው ማንም ሰው ሊመለከቷው ይችላል” ይላሉ፡፡
ከገዳሙ ገቢ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ኪሳቸውን ሲያደልቡ የቆዩት ሰዎች የአዲሱ ሰበካ ጉባኤ እድሜ እንዳይራዘም ቀን ከሌት በመስራታቸውና ገዳሙን ለማስተዳደር በተሾሙት አዲስ አመራር ውጥናቸው ተቀባይነት በማግኝቱ በ2003 ሐምሌ ወር ሰበካ ጉባኤው እንዲፈርስ ተደረገ፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ገዳሙ ያለ ሰበካ ጉባኤው እንዲቀር በመደረጉ ምዕመናን በገዳሙ የሚያበረክቱትን ገንዘብ ንዋየ ቅዱሳትን ሌሎች ስጦታዎችን የት እንደሚያደርሱት በውል ለማወቅ ሳይቻል ቆይቷል፡፡ የገዳሙ አጥቢያ ምዕመናን የገዳሙ መመዝበርን እንደ እግር እሳት የለበለባቸው ጥቂት ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም በሰንበት ተማሪዎች አዲስ ምርጫ ተደርጎ ሰበካ ጉባኤ እንዲመረጥ ያደረጉት ትግል ፍሬ አግኝቶ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ከፓትርያርኩ ጽ/ቤት ምላሽ አገኝ፡፡
ነገር ግን ህዝቡ የሃይማኖቱ ቃለ አዋዲ በሚያዘው መሰረት በመጀመሪያ አስመራጮችን ምርጫ በግልጽ ተደርጎ በቀጣዩ የሰበካ ጉባኤ አባላት በድምጽ ብልጫ ወይም በሌላ መንገድ  ሁሉንም በሚያሳትፍ መልኩ እንደሚመረጥ ሲጠበቅ የገዳሙን ገቢ ሲቆጣጠሩ የነበሩት የሥራ ኃላፊዎች ከምዕመናኑ እውቅና ውጪ የምርጫ ካርዶችን በማዘጋጀት በምርጫው እንዲሳተፉ  ለሚፈልጓቸው ሰዎች ብቻ እንዲታደል ያደርጋሉ፡፡ መረጃው የደረሳቸው የገዳሙ ተቆርቋሪዎችም ምርጫው ይደረግበታል በተባለበት እለት በነቂስ በመውጣት ምርጫ ይደረግበታል የተባለውን አዳራሽ  ያዙ ፡፡ 

ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በገዳሙ የሚደረገውን ምርጫ እንዲታዘቡና ሂደቱን እንዲመረምሩ ተወክለው የተላኩት አባ አዕምሮ ወደ አዳራሹ ከመዝለቃቸው አስቀድሞ የመጡበትን ምክንያት በማብራራት ህዝቡን ለምርጫ ይጋብዛሉ ፡፡ ነገር ግን ህዝቡ ምርጫ ከመከናወኑ በፊት ጥያቄ አለን በማለት ጥያቄ ያቀርባል፡፡ አባ አዕምሮ ጠንከርና ጫን ብለው “ጥያቄ አልቀበልም” በማለታቸው ግርግር ተፈጠረ በዚህ ወቅት የህዝቡ ሁኔታ ያላማራቸው የሀገረ ስብከቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ አባ አዕምሮ እየሮጡ ወደ አዳራሹ ይዘልቃሉ፡፡
ጥያቄያችን ይመለስ የሚሉ ወደ ውስጥ አትዘልቁም በማለት በመከላለከል በነበሩት የስራ ኃላፊዎች ማለትም በገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ ፤ ሂሳብ ሹም ፤ ዋና ጸሀፊ ፤ ምክትል ጸሀፊ ፤ ቁጥጥርና ገንዘብ ቤት መካከል ጭቅጭቅ ይፈጠራል፡፡ ከገዳሙ ሊቀ ዲያቆናት ጌታሁን ወደ ህዝቡ ድንጋይ መወርወር መጀመሩም የጸሎት ቤቱን የተለየ መልክ እንዲይዝ አድርጓል፡፡ በወቅቱ የሁሉንም ትኩረት የሳበውና ድንጋጤ የፈጠረው ከአስተዳደር ኃላፊዎች አንዱ የሆኑት ቄስ  ሽጉጥ መዝዘው ማውጣታቸው ነበር ፡፡

 ሽጉጡን መዥርጠው ሲያወጡ ብዙ ሰዎች እጅጉን ግርምታ ውስጥ እንደገቡ ለማወቅ ተችሏል ፤ የሕግ አስከባሪ አባላት በቦታው በመገኝታቸው ነገሩ ወደ ሌላ ምዕራፍ እንዳይሸጋገር ማድረግ ችለው ነበር ፤ ፖሊሶች በስፍራው በመገኝት ነገሩን እንዲበርድ ካደረጉ በኋላ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተወክለው የመጡት አባ አዕምሮ ለድርጊታቸው ህዝቡን በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡
ቸር ያሰማን

No comments:

Post a Comment