Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, April 5, 2012

የአማራ ተወላጆችን በግዳጅ ወደ መጡበት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ተወገዘ

  ኢሳት ዜና:-በደቡብ ክልል በቤንቺ ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ይኖረ የነበሩ ከ20 እስከ 80 ሺ የሚጠጉ የአማራ ተወላጆች ለአካባቢው ህዝብ አደጋ ናቸው ተብለው እየተፈናቀሉ መሆናቸውን በአገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ ጋዜጦች ሰፊ ትኩረት ሰጥተው በመዘገብ ላይ ናቸው። በዛሬው እለት ለንባብ የበቃው ሰንደቅ ጋዜጣ ይዞት በወጣው ዘገባ ተፈናቃዮች በግዳጅ ወደ መጡበት እየተመለሱ መሆኑን ፣ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ( ብአዴን) ተፈናቃዮችን በማጓጓዝ ሀላፊነቱን ከመላው የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ( መኢአድ) መቀማቱን ዘግቧል። ተፈናቃዮቹ ግን  የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ብቻ ወደ ትውልድ ቦታቸው እንዲመለሱ መደረጉን እየተቃወሙ ነው። በህገወጥ መንገድ ሰፍረውበታል በተባለው አካባቢ ቡና እና ሌሎች ቋሚ ፍራፍሬ ተክሎችን፣ ቤትና ንብረት ትተው መምጣታቸው ከግምት ገብቶ ጊዜያዊ መቋቋሚያ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ ቢሆኑም መንግስት ግን መፍትሄ አልሰጣቸውም።
በአዲስ አበባ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ

አሁንም በአዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 8 በወጣቶች ማዕከል ውስጥ 70 የሚደርሱ ተፈናቃዮች በቂ መረጃ የለም ተብለው ለመቀመጥ መገደዳቸውን ገልጠዋል። ሚሚ የተባለች አርሶ አደር ደግሞ 50 ብር ለትራንስፖርት ሰጥተው ወደ መጣችበት ቀየ እንደተላከች ገልጣለች። በጋዜጣው ዘገባ መሰረት እስከአሁን ከተፈናቀሉት በላይ እንፈናቀላለን ብለው የሰጉ በርካታ በርካታ የአማራ ተወላጆች አሉ። ለአቤቱታ ወደ አዲስ አበባ የመጡት አርሶአደሮች በዚያው ያለምንም ክፍያ ወደ ተወለዱበት ቀየ እንዲመለሱ መደረጋቸው የሌሎችን ስጋት ጨምሮታል።  በ1999 ዓ.ም ወደ አካባቢው የገቡ የአማራ ክልል ተወላጆች ‘‘ውጡ’’ ከተባለ ለእኛም አይቀርልንም ብለን የሚሰጉት አቶ ተፈሪ ከብቶቻቸውንም ወደ ዱር ለማሰማራት መቸገራቸውን ያስረዳሉ። ‘‘መሳሪያ አስረክቡ’’ በመባሉም ከብቶቻችንን ወደግጦሽ ማሰማራት አልቻልንም ሲሉ ለጋዜጣው ሪፖርተር ገልጠዋል። ‘‘ተፈናቃዮቹ ልቀቁ’’ የተባሉት መሬቱን ‘‘ለተወላጆቹ ልቀቁ’’ በመባሉ መሆኑን አቶ ተፈሪ ይናገራሉ።  ‘‘መብት አጣን እንጂ መሬቱ ይበቃን ነበር’’ የሚሉት አቶ ተፈሪ ለቀው በወጡት ሰዎች ምትክ የአካባቢው ሰዎች እየተተኩ አለመሆኑንም ገልፀዋል። ከአካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎች 8ሺህ ብር የሚያወጣውን በሬ በ3ሺህ ብር እየሸጡ ለመውጣት ተገደዋል ሲሉ አክለዋል።

ፍኖተ ነጻነት ዛሬ ባወጣው ዘገባ ደግሞ የተፈናቃዮች ቁጥር ከ80 ሺ እንደሚበልጥ ዘግቧል። ሪፖርተር ህገመንግስትና ህግ የማይስማሙባት አገር በሚል ባወጣው ዘገባ ደግሞ ” ስለጉርዳፋ ወረዳ አመሰራረት እንዲህ ሲል ዘግቧል ” በ1993ዓም በፊት በደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን ውስጥ ጉርዳፋ ተብሎ የሚጠራ አልነበረም። በአሁኑ ወቅት በጉርዳፋ ወረዳ የሚተዳዳሩት የሚኒጥ ብሄረሰቦች ከ1993ዓም በፊት ይተዳደሩ የነበሩት በሸኮ ወረዳ ስር ነበር። እነዚህ ብሄረሰቦች “በሸኮ ወረዳ ስር አንተዳደርም ራሳችንን በራሳችን ማስተዳደር አለብን” የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ራሳችሁን በራሳችሁ ለማስተዳደር መስፈረቱን አታሟሉም ሲባሉ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል  ደቡብ ክልል ውስጥ በተለያዩ ወረዳዎች በቡና ለቀማና በተለያዩ የጉልበት ስራዎች የተሰማሩ በርካታ የአማራ ክልል ተወላጆችን ” ወደ እኛ ወረዳ መጥቶ በልማት ስራ ላይ መሰማራት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሙሉ ይምጣና አካባቢውን ያልማ” የሚል ማስታወቂያ ለጥፈዋል። የቀበሌና የወረዳ አመራሮችም መሬት በህጋዊ መሬት በመስጠት በቂ የህዝብ ብዛት አግኝተው ራሳቸውን ማስተዳደር መጀመራቸውን ፣ ወረዳቸውም ጉራዳፋ መባሉን ገልጧል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አርሶአደሮቹ ምድረበዳ የነበረውን አካባቢ መለወጣቸውን ጋዜጣው ገልጧል።

የደቡብ ክልል ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት ከ1999ዓም በሁዋላ በጉራፋርዳ የሰፈሩ የአማራ ተወላጆች በህጋዊ መንገድ ያገኙትን መሬት እንዲለቁና አካባቢውን ጥለው እንዲሄዱ ፣ ውሳኔውን ተከትሎም ጥረው ግረው አካባቢውን ያቀኑ በብዙ ሺህ የሚገመቱ ነዋሪዎች በሀይልና በጉልበት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉንም፣ አሁንም እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ፣ ይህ ሁሉ ሲሆን የፌደራል መንግስት ሆነ የአማራ ክልል ባለስልጣናት አንድም ነገር ትንፍሽ አለማለታቸውን ፣ አቤቱታ ለማቅረብ ባለፈው ሀሙስ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ተፈናቃዮችም ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ በአራት አውቶቡሶች እና በአንድ ሚኒባስ ታጭቀው ወደ ደብረብርሀን መጓዛቸውንና ሰዎቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አለመታወቁን ጋዜጣው ዘግቧል። የኢዴፓ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ሙሼ ሰሙ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ዜጎችን የማፈናቀል እርምጃ ከየአካባቢው የሚመነጭ ከሆነ የአትዮጵያዊነት ትርጉሙ ምንድነው ሲሉ ጠይቀው፣ አንድ ዜጋ እንደ ዜጋ ዳር ድንበርን የማስከበር ጥያቄ ጥሪ ሲቀርብለት ጥሪውን ተቀብሎ የህይወት መስዋትነት የሚከፍለው በማንኛውም ክልል ላይ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት አለኝ ብሎ ስለሚያም ነው። አለበለዚያ ጉዳዩ የተወረረው ክልል ጉዳይ ብቻ ይሆናል። ወደ ፊት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በማስከበር ረገድ የራሱን ችግር ይፈጥራል ሲሉ አክለዋል በማለት ጋዜጣው ዘግቧል። አቶ መሳይ በቀለ ደግሞ በራስህ አገር ውስጥ እንዴት ስደተና ትሆናለህ?’ ሲሉ ጠይቀው ዜጎች የሌላ ብሄር አባላት ስለሆኑ ብቻ ይኖሩበት የነበረውን ቀየ እንዲለቁ ማድረግ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል።

የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው ፍኖተ ነጻነት ዛሬ ዜጎችን የማፈናቀልና የማባረር ተግባር በአስቸኳይ ይቁም በሚል ርእስ ባወጣው ርእሰ አንቀጽ ደግሞ ” ኢህአዴግ ላለፉት 20 አመታት ዘርቶ እያጨዳቸው ካሉ አስከፊ ፍሬዎቹ አንዱ ይሄው መርዛም የጎሳ ፖለቲካ ነው። ኢትዮጵያዊው በሀገሩ እንደ መጻተኛ እንዲኖር የሚያደርገው ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚፈታተንና የሚሞግት የዘመናችን እዳም ይሄው ነው። አለማችን ወደ አንድ መንድር እየተለወጠች ባለችበት ጊዜ በሀገራችን አንዱ አትዮጵያዊ ወደ ሌላው የኢትዮጵአ ክፍል ሂዶ የመኖር መብቱ ተገፏል።” ብሎአል። አንድነት ፓርቲ አክሎም ” እኛ ይሄ ሰብአዊ መብት መገፈፉን እናወግዛለን፣ ህዝብን ንብረት የማፍራት መብቱ መነጠቁን እንኮንናለን። ዜጎችን የማፈናቀል እና የማባረር ተግባርንም አጥብቀን እንቃወማለን። ከላይ እግር አውጥቶ ሲሄድ እያየነው ያለነው መርዛም ብሄርተኝነት በተለይ በደቡብ ክልል መንግስት እየተፈጸመ ያለው ተግባር የኢህአዴግ የፌደራሊዝም አስፈሪ ገጽታ ነው። የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በተለይ የአማራ ተወላጆች የሆኑ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን እንደ ምናምንቴ ነገር ጠርገው አስወጥተዋል። አባት እናት አሮጊት ሽማግሌ ህጻናት ሳይለይ ያፈሩትን ሀብትና ንበረት በወጉ የሚሸጡበት እድል ሳይሰጣቸው ፣ ያለሙትን መሬት ጥለው እንዲወጡ ተደርገዋል። በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ደብዳቤም ድንበር ሰብሮ እንደገባ ህገወጥ ዜጋ ተቆጥረው እጅና እግራቸውን ይዘው ሲወጡ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ራሳቸው ህገመንግስቱን የጣሱ ህገወጦች ናቸው አሉ። እንዲህ አይነቱን ኢሰብአዊ የሆነ ተግባር አንደነት ፈጽሞ አይታገሰውም።” ብሎአል።

ግንቦት 7 ለኢሳት በላከው ልዩ መግለጫ ደግሞ “መለስ ዜናዊ “የኢትዮጵያን አጥፍቼ ልጥፋ” ስትራቴጂ ሰሞኑን በሙሉ ኃይሉ ሥራ ላይ እየዋለ ነው። ከዓመታት በፊት በመንግሥት ውትወታ በደቡብ ክልል ሰፍረው የነበሩ የአማራ ዝርያ ያላቸው አርሶ አደሮች ወንጀለኞች የሆኑ ይመስል ንብረታቸው ተዘርፎ እንዲባረሩ ወያኔ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት እየደረሰባቸው ያለው ግፍ ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሆኗል ብሎአል። ንቅናቄው  በአማራ አርሶ አደሮች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የወያኔ ዘረኝነት ፓሊሲ ውጤት መሆኑን ብቻ ሳይሆን  እርምጃዉ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጦ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና  የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከተገፉትና ከተሰደዱት የአማራ ገበሬዎች ጎን አንዲቆም ጥሪ አድርጓል።

ግንቦት 7 አክሎም “አማራውን እወክላለሁ የሚለው የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የመለስ ዜናዊ ምርጥ ባርያ ለመሆን ሲል በአማሮች ላይ ዘምቷል። ብአዴን የወያኔን ጥቃት አቀነባባሪና አስፈፃሚ ሆኗል። ሌላው ቀርቶ ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ድሃ አርሶ አደሮች አዲስ አበባ ከተማ እንዳይገቡ ከመንገድ እያፈሰ ወደ ማጎሪያ እስር ቤቶች የሚልከው ብአዴን ነው። ወያኔ በመላው ኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ላይ እንዲፈነጭ ብአዴን የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። ስለሆነም በአማራ ላይ እየተፈፀመ ላለው ወንጀል ብአዴንም ቀንደኛ ተጠያቂ ነው። በጥንታዊው እና ታሪካዊው የዋልድባ ገዳም ላይ እየተደረገ ያለው ጥቃትም ከዚሁ ጋር መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ዋልድባ በዶዘር መታረስ ጀምሯል። አቤት ለማለት የቃጡ አርሶ አደሮችና መነኮሳት በመለስ ዜናዊ ቅጥረኖች ተንገላተዋል። ይህ ሃይማኖትን፣ ቅርስን፣ ታሪክን መድፈር ነው። አማራ የእርሻ መሬቱ ተነጥቆ ከፊሉ ለትግራይ፣ ከፊሉ ለሱዳን፣ ከፊሉ ደግሞ ባህር ተሻግረው ለመጡ ቱጃሮች ተከፋፍሏል። ድሃው አማራ ምን ይሁን? እውን እኛስ ከዚህ በላይ ምን እስክንሆን ነው የምንጠብቀው? በማለት ጠይቆ ፡ በወያኔ ወገኖቻችንን ከመኖሪያ ቀያቸው የማፈናቀል ዘመቻ ሳቢያ ከጉራ ፈርዳ ወረዳ እንዲፈናቀሉ ከተደረጉ የአማራ ወገኖቻችን በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከ70 ሺህ በላይ የአፋር ወገኖቻችንም ከትውልድ መንደራቸው በወታደር ኃይል መባረራቸውን ዛሬ በአማራ አርሶ አደሮች ላይ የደረሰው ከይዞታቸውና ከቄያቸው መፈናቀል ትናንት በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ መደርሱን አስታወሷል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ነገ ሁላችንም ተነሽዎች ፤ ሁላችንም ተሳዳጆች ነን  በማለት እርምጃውን አውግዞ ህዝቡ ለስርአት ለውጥ እንዲነሳ ጠይቋል።

No comments:

Post a Comment