Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Tuesday, October 23, 2012

በገርባ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በርካታ ወጣቶች እየታሰሩ ነው



Gerba town killing in South Wollo
ኢሳት ዜና:-የፌደራል ፖሊስ አባላት 4 ንጸሁን ዜጎችን ፣ ሁለቱን አስረው በመውስድና በመረሸን ሁለቱን ደግሞ በተቃውሞው ቦታ ላይ ከገደሉ በሁዋላ ፣ ሌሊቱን የቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ በርካታ የገርባ ቀበሌ ወጣቶችን ማሰራቸው ታውቋል። 

ትናንት ምሽት በርካታ ወጣቶች ከተደበቁበት ቦታ በመሆን ስልኮችን ወደ ኢሳት ቢሮ እየደወሉ የፌደራል ፖሊስ አባላት ቤቶችን እያስከፈቱ ሲሰፈትሹ እንደነበር ድምጻቸውን ዝቅ በማድረግ ሲናገሩ አምሽተዋል። እስካሁን ድረስ የታሰሩትን ሰዎች ቁጥር በውል ለመለየት ባይቻልም፣ የ106 ሰዎችን ዝም ዝርዝር የያዙ የፌደራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ በአህባሽ አስተምህሮ ተከታይነታቸው ከሚታወቁ ሰዎች ጋር በመሆን ቤቶችን እየፈተሹ አንዳንድ ወጣቶችን ይዘው አስረዋል።


የታሰሩ ሰዎችን ስም ዝርዝር በማጠናቀር  ላይ ያሉ የአካባቢው ወጣቶች እንደገለጡት እስካሁን ድረስ ባጠናከሩት መረጃ እስማኤል አብዱ አዎል፣ አብዱላሂም፣ ኡስማን አህመድ፣ ሼህ አብዱ፣ አህመድ ዳሊ ፣ ኑሩ አህመድ፣ ሳሊም ኬሌና አብዶ አህመድ የተባሉ የገርባ ነዋሪዎች ታስረዋል። የእስረኞች ቁጥር ግን ከዚህም አሀዝ እንደሚበልጥ በእርግጠኝነት ተናግረዋል።

በገርባ ቀበሌ ዛሬ የፌደራል ፖሊስ አባላት ነዋሪውን ስብሰባ በመጥራት በችግሩ ዙሪያ ውይይት አድረገዋል። ፖሊሶቹ በተቃውሞ የተሳተፉትን ወጣቶች ህብረተሰቡ አሳልፎ እንዲሰጥ መጠየቃቸው ታውቋል። ይሁን እንጅ አብዛኛው የቀበሌው ወጣት አካባቢውን በመልቀቅ ወደ ገጠር አካባቢዎች ተስዶ የተደበቀ በመሆኑ በስብሰባው ላይ የተሳተፉት ጥቂት በእድሜ የገፉትና ከመንግስት ጋር በጋራ ስራ የሚሰሩ የአህባሽ አስተምሮ ተከታዮች ብቻ ናቸው ሲሉ ነዋሪዎች ገልጠዋል። በዚሁ ዙሪያ የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በሌላ በኩል ደግሞ ግንቦት7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ መንግስት በገርባ ህዝብ ላይ የወሰደውን እርምጃ አውግዟል። ” ኃይለማርያም ከመድረሱ፤ የንፁሃንን ሕይወት መቀንጠሱ!!! ” በሚል ርእስ ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ ” አቶ ኃይለማርያም የመለስ ዜናዊን “ሌጋሲ” ለማስፈፀም ቃል እገባለሁ ያለው ለካስ ኢትዮጵያዊያንን በግፍ የመጨፍጨፍ ሌጋሲ  ነበር፣  እንደተናገረውም  “የመሪውን ሊጋሲ” የሚያስቀጥል መሆኑን ከጅምሩ እያሳየን ነው ብለኦል።

ግንቦት 7 በመግለጫው ” በወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ከገለጸ በሁዋላ ፣ ለሟቾቹ ጀነትን ለቤተሰቦቻቸው ደግሞ መጽናናትን ተመኝቷል። እነዚህ ውድ ኢትዮጵያዊያን ለመብቶቻቸው መከበር ሲሉ ከፍተኛውን የሕይወት መስዋትነት የከፈሉ ሰማዕታት አድርጎ እንደሚመለከታቸውን ንቅናቄው አክሎ ገልጧል።

አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ፣ እውነተኛ ሥልጣን ኖረውም አልኖረው ለገዢው ፓርቲ በምስለኔነት ለመሥራት ፈቅዶና ወዶ ገብቶበታልና በወገኖቻችን ደም ቀጥታ ተጠያቂ ነው ብሎ ግንቦት 7 እንደሚያምን ገልጧል።

የይስሙላም ቢሆን ገና በሥልጣን ወንበር ላይ እንደተቀመጠ የንጹሃንን ደም ማፍሰሱ አቶ ኃይለማርያምን ልክ እንደ አቶ መለስ ዜናዊ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ኢትዮጵያ ያደርገዋል ሲልም ኮንኗል።

ግንቦት 7 በመጨረሻም  ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እስካሁን በሰላማዊ መንገድ አገዛዙን ለማስገንዘብና ለማንቃት ያደረጉትን ተጋድሎ አድንቆ ከእንግዲህ ግን የማስገደዱ አለያም የማስወገዱን ሥራ በተቀናጀ መንገድ ካልሰራነው በስተቀር የሕዝባችን መገደል፣ መደብደብና መረገጥን ማስቆም አንችልም። ስለሆነም ግንቦት 7፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ – ሙስሊሙም ክርስቲያኑም – ለሰብዓዊ መብቶታችን መከበር በጋራ እንዲነሳ ጥሪ ያደርጋል።”  ብሎአል

የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው ሶስት ሰዎች የተገደሉት አክራሪዎች ፖሊስ ጣቢያውን በመስበር ፖሊስ የያዛቸውን ጓደኞቻቸውን ለማስለቀቅ ሙከራ ሲያደርጉ ነው በማለት ለሮይተር ገልጸዋል።
ኢሳት ትናንት እንደዘገበው ከተገደሉት 4 ሰዎች መካከል 2ቱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በሁዋላ ነው የተገደሉት። የኢትዮጵያ ህግ መንግስትም ሆነ አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ሰዎች ከተያዙ በሁዋላ ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው ቢደነግግም ፖሊስ ግን ይህን በመጣስ በቁጥጥር ስር ባዋላቸው ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ መንግስትን አንድ ቀን በህግ የሚያስጠይቀው ይሆናል በማለት ኢሳት አነጋገራቸው አንድ የህግ ባለሙያ ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment