Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, August 3, 2012

ሀገሪቱ በማን እየተመራች ነው?, በብስራት ወ/ሚካኤል

ሰው ከዚህች ዓለም ፍጡር አንዱ ብቻ ሳይሆን መኖሪያቸውን በምድር ያደረጉትንም እንዲገዛና እንዲጠቀም የተፈቀደለትም ጭምር ፍጡር ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን እንደሚዋለድ እንደሚያድግ እና እንደሚሞት መረሳት የለበትም፤የሰው ልጅ ሟች ነውና፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ የገዥው ቡድን መሪዎች ግን ብዙዎች ተሰውተው እዚህ የደረሱ መሆናቸው እንኳ ያሰቡት አሊያም የሚያስቡት አይመስልም፡፡እነኚህ ሰዎች ደግሞ ከታሪክና ትውልድ ሳይሆን ከአደጋ እንጂ ከሌላ መማርን የሚፈቅዱ መስልም፡፡ 


ለዚህም ነው ብዙ የሚዘምሩለት፤ ሲያሻቸው በሰበብ አስባቡ ተቀናቃኞቻቸውን፣ ለሀገርና ለህዝብ የሚያስቡትን ንፁሃን ለመወንጀል የሚጠቀሙበት “ህገ መንግስት” ብዙ ክፍተቶችን ይዞ የሚገኘው፡፡ ሲያዜሙለት ግን ህገመንግስቱ ያልመለሳቸው ጥያቄዎች የሉም ቢሉም እጅግ ብዙ ጥያቄዎች ያለመመለሳቸው ይልቁንም ዝግ የሆኑ ብዙ ቢኖሩም ለአሁኑ ግን ወቅታዊውን አንዱን ጉዳይ እንይ፡፡
 
በመሪዎች ጉዳይ የተቀመጠ  ህጋዊ ማዕቀፍ አለመኖር የእኛ ሀገር መሪዎች ራሳቸውን ታማሚና ሟች መሆናቸውን አምነው የመቀበል ባህሪ አይታይባቸውም፡፡ ይልቁንም ራሳቸውን ዘለዓለማዊ (መለኮታዊ) ባህሪ የተላበሱ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ አምባገነን፣ በሙስና የተዘፈቀ፣ ሁሉን ነገር እሱ ብቻ አዋቂ አድርጐ የመቁጠር ክፉ አባዜ ይፀናወታቸዋል፡፡

በኢትዮጵያም በአሁን ወቅት ሥልጣናቸውን ዘለዓለማዊ ዙፋን አስመስለውት ያሉት ከላይ ከተጠቀሱት የተለየ ባህሪ አይታይባቸውም፡፡ ለዚህም ይመስላል በህገ መንግስቱ ላይ እንኳ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር አሊያም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢታመሙና ቢሞቱ ማን እንደሚተካቸው በግልጽ የተቀመጠ ነገር የሌለው፡፡ በቅርቡ ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዘዳንቱ) ታመው ነበር፡፡ ከስራቸው ግን ህጋዊ ማዕቀፍ ያለው ምክትል ፕሬዘዳንት የለም፡፡ ነገር ግን በየዕለቱ (ምናልባት ካልደበቋቸው) የተለያዩ ተፈፃሚነት ያላቸውና የሚፈፀሙ ሀገራዊ ጉዳዮች እሳቸው በታመሙ ወቅት ማን ፈርሞ እንዳፀደቃቸውና ህጋዊ እንዳደረጋቸው አይታወቅም፡፡

ርዕሰ ብሔሩ የስራ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ቢያልፉ እንኳ ማን እና ሌላ እንዴት እንደሚተካ አሁንም ድረስ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ በየዕለቱ ግን እንግዳ መቀበልና መሸኘትም ይሁን መፈረም የተለያዩ የሚሰሩት ስራ ይኖራል፡፡ የሚዜምለት ህገ መንግስት ግን በመሪዎች “ብልጣብልጥነት” ይሁን ዝርክርክነት ስለዚህ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ ሀገሪቷን በህገወጥ መንገድ ሌላ ሊተካ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የመንደር ማፍያዎች ስራ እንጂ የሀገር መሪዎች ስራ ሊሆን አይችልም፡፡

ሰሞኑን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታመው ልክ ጫጉላ ቤት(ሙሽራ) ሆነው የተቀመጡ ይመስል ለረጅም ጊዜ ተደብቆ ቆየ፡፡ በርግጥ እሳቸው የታመሙት ሰሞኑን ሳይሆን ድሮም ሙሉ ለሙሉ ጤነኛ ነበሩ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም በተለያየ ጊዜ በሀገሪቱና በህዝቡ እንዲሁም በመንግስታቸው ላይ በርካታ ስህተቶችን ፈፅመዋል፡፡ ለምሳሌ ንፁሃንን በድፍረት ባልተረጋገጠ ነገር
ወንጀለኛ በማድረግ በፍ/ቤቶች ላይ ጫና መፍጠር፣ የሀገሪቱንና የህዝቡን ጥቅም የባህር በር (የአሰብ ወደብን)፣ ባድመንና የመሳሰሉትን ለሌላ አሳልፈው የመስጠት፣ በየመድረኩ መሳደብ፣… የመሳሰሉት፡፡ እነኚህ ድርጊቶች ደግሞ በህመም እንጂ በጤንነት የተፈፀሙ ናቸው ለማለት ያስቸግራል፡፡

ይሁን እንጂ የእሳቸው መታመምና የአልጋ ላይ ዕረፍት ከፈጣሪ/ከዶክተሮች የተበየነባቸው አሜሪካ በተካሄደው የቡድን 8 አባል ሀገራት የጋራ ውይይት መድረክ ላይ በተደረገው ስብሰባ ወቅት ከጋዜጠኛ
አበበ ገላው የተላከ መብረቅ ድምጽ በኋላ ነው፡፡ በወቅቱ የጋናው ፕሬዘዳንት ጆን ኢቫንስ አታ ሚልስ አብረዋቸው በመድረኩ የተጋበዙ ቢሆንም አቶ መለስ ዜናዊ ላይ የአበበ ገላው አስደንጋጭ የተቃውሞና የውግዘት ናዳ ሲወርድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደንግጠው አንገታቸውን ሲደፉ፤ ከጐን ያሉት የጋና አቻቸው ራሳቸውን እየነቀነቁ ይታዘቡ እንደነበር አይተናል፡፡

የሚገርመው ግን ባራክ ኦቦማን ጨምሮ የበለፀጉ ሀገራትን መሪዎች ያስደመመው የአበበ ገላውና የአቶ መለስ ዜናዊ የመድረኩ ከስተት የጋና አቻቸውንም ያስደነገጠ ሲሆን በቅርቡ እኚሁ ከአቶ መለስ ጐን ተቀምጠው የነበሩት የጋናው ፕሬዘዳንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፤ነፍሳቸውን ይማረውና፡፡ የኢትዮጵያው አቶ መለስ ዜናዊ ደግሞ ከነ አቶ በረከት ስምዖን በተሰጠው መግለጫ ግን አቶ መለስ መታመምና ዕረፍትም እንደሚያስፈልጋቸው በዶክቶሮቻቸው እንደተነገራቸው ይፋ ተደርጓል፡፡

አቶ መለስ ዕረፍት እንደሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ ህዝብና ተቃዋሚዎች ደጋግመው የነገራቸው ቢሆንም “ፓርቲዬ ስለመረጠኝ ነው” በሚል ፈሊጥ ያለዕረፍት የ4 ኪሎውን ቤተመንግስት “የሙጢኝ፣ አልለቅም” በማለታቸው ለዚህ ደርሰዋል፡፡ ታዲያ ለእሳቸው የጤና ህመም ተጠያቂው ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ነው? ወይንስ ጋዜጠኛ አበበ ገላው? ወይንስ ራሳቸው? እንደኔ እንደኔ ተጠያቂው የአራት ኪሎ ጉልቻ ያደረጋቸው ፓርቲያቸው አሊያም ራሳቸው ተጠያቂ መሆን አለባቸው፤ መጠየቅ ካለበት፡፡ አሁንም ቢሆን አቶ መለስ ታመው ስራ እየሰሩ እንዳልሆነና መስራትም እንደማይችሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከመንግስታቸው በተሰጠ መግለጫ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ታዲያ አሁን ሀገሪቱ በማን እየተመራች ነው? አቶ በረከት ስምዖን ለጋዜጠኞች መመለስ ያልቻሉትና መመለስም ያልደፈሩት በአሁን ወቅት ሀገሪቱ በማን እየተመራች እንደሆነ የሚለውን ነው፡፡ ለዚሀ ዋናው ምክንያት ደግሞ የመጀመሪያው የሚሾሙት አሊያም የሚመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ቢታመሙ አሊያም ቢሞቱ “በዚህ ደረጃ ላይ ያለ ተክቶ ይሰራል” የሚል ግልጽ የሆነ ህጋዊ ማዕቀፍ ያለመኖር ነው፤ የምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው ከሚለው በቀር፡፡

በአሁን ወቅት ደግሞ በኢህአዴግ ካምፕ ውስጥ የእሳቸውን ቦታ ለመያዝ እየተፈጠረ ነው የሚባለው የስልጣን ሽኩቻ የትኛው ጐራ መጥቆ እንደወጣና መንበረ ስልጣኑን ማን እንደተቆጣጠረው ግልጽ አልሆነምና ነው፡፡ እዚህ ላይ ሀገሪቱ በማን እየተመራች ነው? ሌላም ግልፅ ያልሆነው የወ/ሮ አዜብ መስፍን ነገር ነው፡፡ እንደወጉና እንደ ባህላችን ቢሆን ባል ሲታመም በዋናነት ከጐን ሆና ምታስታምመውና በህመም ወቅት ምስጢራዊ ግንኙነት የሚኖራት የልቡንም የምትሞላው ሚስት ነበረች፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ግን ለዚህ የታደሉ አይመስሉም፡፡ ምክንያቱም ባለቤታቸው እንደሆኑ የሚታወቁት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ያሉት አዲስ አበባ 4 ኪሎው ቤተ መንግስት ውስጥ ነውና፡፡ አቶ መለስ ግን ህክምናቸውን እየተከታተሉ ያሉት በውጭ ሀገር እንደሆነ ይነገራል፤ ሌላ የሚናፈስ ወሬ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡

የአቶ መለስ በውጭ ሀገር ህክምናቸውን እየተከታተሉ ነው መባሉና የወ/ሮ አዜብ መስፍን አዲስ አበባ መኖር በራሱ በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ የመጀመሪያው አቶ መለስ ባለቤታቸው ከጐናቸው እንዳይሆኑ የተፈለገው እንደ ባለቤት አያምኗቸውም፡፡ አሊያም አይወዷቸውም ወይንም ባለቤታቸውንም ይፈራሉ ወይንም ይጠራጠራሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እስካሁንም ምናልባት ልጅ ከመውለድ ባለፈ የባልና ሚስት ወግ አልነበራቸውም ማለት ነው፡፡

ሌላው የወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተመንግስት መቆየት የሀገሪቱን የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ ነው አሊያም በእሳቸው አለመኖር ስልጣናቸው ላይ አደጋ እንዳይፈጠርና ምናልባት ድነው የሚመጡ እንኳ ቢሆን ጓዶቻቸው አየር ላይ እንዳያስቀራቸው በመፍራት የስልጣን (የወንበር) ዘብ አድርገዋቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አቶ መለስ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉትን ማናቸውንም ባለስልጣናት እንደማያምኗቸው፤ ባለስልጣናቱም በሳቸው መረብ ውስጥ የተጠመዱ ሞኛሞኝ አሳዎች እንጂ በራሳቸው የሚተማመኑ አለመሆናቸውን ይገልፃል፡፡

በርግጥ አቶ መለስ ጥላቸውንም እንደማያምኑ ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ እሳቸው በስልጣን ህይወት ዘመናቸው ለሀገሪቱ ህዝብ፣ ለተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን ለኢህአዴግ አመራር አባላትም ምን ያህል ክፉ እንደነበሩ የሚያሳብቅ ይሆናል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የወ/ሮ አዜብ አዲስ አበባ መኖር አቶ መለስ እስከ ወዲያኛው አርፈው ይሆን እንዴ? የሚያስብል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ምክንያቱም ባለቤታቸው ታመው እንዴት ቢጨክኑ ነው ወ/ሮ አዜብ አዲስ አበባ የሚቀመጡት? ያስብላልና፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያዊ ባህል፣ እንደ ጥሩ ሚስት እና እንደ ሴት ተፈጥሮአዊ ባህሪ ባል ታሞ በውጭ ሀገር እየታከመ ሚስት ተንደላቃ አዲስ አበባ መቆየት የማይታሰብና አምኖ ለመቀበል የሚከብድ ነገር ነው፡፡

በዚህ ጽሁፍ የመጨረሻው ግምት የወ/ሮ አዜብ ባለቤታቸው ታመው በውጭ ሲታከሙ የእሳቸው አዲስ አበባ መሆን የአቶ መለስን መታመም ተከትሎ በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ መጥቆ የወጣው አካል አግቶ የቁም እስረና አድርጓቸውም ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ግምቶች እንዳሉ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱን በመወከል በየዕለቱ በርካታ  ነገሮች እንደሚያከናውኑ ይጠበቃል፡፡ በዋነኝነትም የተለያዩ የትብብር፣ የብድር እና የእርዳታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሰነድ ላይ መደራደርና ማፅደቅን ጨምሮ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች እሳቸውን የሚጠብቁና የሚመለከቱ አሉ፡፡

ታዲያ በዚህ ሁኔታ በአሁን ወቅት አቶ መለስ በሌሉበት በህጋዊ መንገድ እሳቸውን ተክቶ የሚሰራ ማን እንደሆኑ እና ማን እየመራው እንዳለ ህዝቡ የማወቅ መብቱ መነፈጉ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እሳቸውን ተክቶ እየሰራ ያለው ማን እንደሆነ ማወቅ ተጠያቂነትን፣ ኃላፊነትንና ምናልባትም
ግልፀኝነት ያለው አሰራርን ያሰፍናል፡፡ 

ነገር ግን በአሁን ወቅት ሀገሪቱን ማን እየመራት እንዳለ አለመታወቁ የአቶ መለስ አሻንጉሊት እንደሆኑ የሚነገርላቸው እና “የመንግስት ሌቦች” የሚባሉት ባለስልጣናት በሚፈጥሩት የወንበር ሽኩቻ በሀገሪቱና በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በአሁን ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስራ በህጋዊ መንገድ ተክቶ እየሰራ ያለው ማን እንደሆነ ስልጣን ላይ ባሉ የሚመለከታቸው አካላት በግልጽ ሊነገር ይገባል፡፡

እዚህ ላይ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ህዝቡም ይህን ማወቅ እንዳለበት መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ እንደ አቶ መለስ ህመም የነ አቶ በረከት መግለጫ “ይሄ የገዥው ፓርቲ የቆየ ባህል ነው” ተብሎ መታለፍ የሚያመጣው መዘዝ የከፋ ሊሆን ስለሚችል ከወዲሁ ነቅቶ መጠበቅና መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ በመሀል በሚፈጠር ክፍተት የሀገሪቱ ሀብትና ንብረት በግልጽም ይሁን በስውር እየተዘረፈ ሊሆን ስለሚችል ተጠያቂነትና ኃላፊነትን የሚወስድ አካል ባለመኖሩ ሆን ተብሎም ይሆን ባለማወቅ ብዙ ስህተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉና ሀገሪቱን ማን እየመራት እንዳለ በግልፅ
መታወቅ አለበት፡፡

No comments:

Post a Comment