Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, August 12, 2012

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፍ በ40 በመቶ ቀነሰ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያተፈረው ትርፍ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ40 በመቶ ቀነሰ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የድሪምላይነር አውሮፕላንን መምጣት አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በቢሮአቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ እ.ኤ.አ በ2011/2012 የበጀት ዓመት አየር መንገዱ የተጣራ 730 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ ተናግረዋል፡፡ አየር መንገዱ እ.ኤ.አ በ2010/2011 በጀት ዓመት ያገኘው የተጣራ ትርፍ 1.23 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ይህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተገኘው ትርፍ በ500 ሚሊዮን ብር ይበልጣል፡፡


አየር መንገዱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  4.6 ሚሊዮን መንገደኞች ማጓጓዙ ተጠቁሞ፣ የ25 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ተገልጿል፡፡  በበጀት ዓመቱ 33.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም የ37 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

አቶ ተወልደ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት እጅግ በጣም ፈታኝ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ120 ዶላር በላይ ተሰቅሎ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ እንደቆየ የገለጹት አቶ ተወልደ፣ የነዳጅ ዋጋ እንደዚህ ንሮ ለረጅም ጊዜ ሲቆይ ለመጀመርያ ጊዜ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹በአውሮፓ የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የእስያና የሌሎች አገሮች ኢኮኖሚ ዕድገት ፍጥነት መቀነስ፣ የአየር ትራንስፖርት ፍላጐት እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አድርጓል፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ በዚህም ምክንያት የኬንያ ኤርዌይስ በቅርቡ የሠራተኞች ቅነሳ እንደጀመረ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በርካታ ዓለም አቀፍ አየር መገዶች ኪሳራ ውስጥ በገቡት ወቅት ይህን ሁሉ ተቋቁመን በሠራተኞቻችን ብርታት ትርፋማ ለመሆን ችለናል፤›› ብለዋል፡፡ አየር መንገዱ ለሠራተኞቹ ከስድስት እስከ ስምንት በመቶ የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ እ.ኤ.አ በ2010/2011 በጀት ዓመት ያገኘው 1.2 ቢሊዮን ብር ትርፍ እጅግ ከፍተኛ እንደነበር አንድ የድርጅቱ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በበጀት ዓመቱ የዶላር ምንዛሪ 20 በመቶ እንዲጨምር ተደርጐ የነበረ በመሆኑ የኩባንያው ትርፍ የተጋነነ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ በዚህ ምክንያት በ2010/2011 በጀት ዓመት የተገኘውን ትርፍ ከ2011/2012 በጀት ዓመት ትርፍ ጋር ማነፃፀር ፍትሐዊ አይሆንም፤›› ብለዋል ኃላፊው፡፡

የደቡብ አፍሪካ ኤርዌይስ ኪሳራ ውስጥ የተዘፈቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት እየተደጐመ ነው፡፡ የሞሮኮ አየር መንገድ በተከታታይ በመክሰሩ ምክንያት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሠራተኞቹን መቀነስ ጀምሯል፡፡ ከአውሮፓም ሉፍንታንዛና ኬኤልኤም ፍራንስ ከከሰሩ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች መካከል እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር በአውሮፓ የኢኮኖሚ ቀውስና በነዳጅ ዋጋ ንረት ምክንያት የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ችግር ውስጥ እንደሚገባ ጠቅሶ የአፍሪካ አየር መንገዶች ደግሞ በድምሩ 100 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከስሩ ተንብዮ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገጠሙትን ችግሮች ተቋቁሞ በዓመት ከ25 እስከ 30 በመቶ በማደግ ላይ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ተወልደ፣ ራዕይ 2025 የተሰኘውን የዕድገት መርሐ ግብር በማሳካት ላይ ነው ብለዋል፡፡ አየር መንገዱ የካርጐ ተርሚናልና የጥገና ሃንጋር ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሆነ  አቶ ተወልደ አስታውቀው፣ በደቡብ አፍሪካና በመካከለኛው አፍሪካ ሁለት ክልላዊ መናኸሪያ (Regional Hub) ለማቋቋም በመሥራት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

No comments:

Post a Comment