Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Tuesday, May 29, 2012

መታወቂያችን አማራ ስለሚል ተመርጠን ታሰርን ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ

 By ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ
ከሚዛን ተፈሪ ወደ ዲማ ለሥራ ስንሄድ ኬላ ላይ መታወቂያ እየተመለከቱ ሲፈትሹ መታወቂያችን ብሔር በሚለው ቦታ ላይ አማራ ስለሚል መርጠው እስር ቤት ከተቱን፡፡ ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን ገለጹ፡፡ እነዚህ እስር ቤት ቆይተን ተፈታን የሚሉ ሰዎች እንደሚሉት “ዲማ በጉልበትህ ሠርተህ የምታገኘው ገንዘብ አለ የሚል መረጃ ስለደረሰን ሥራ ፍለጋ በመጓዝ ላይ ነበርን፡፡ ሚዛን ተፈሪ ስንደርስ ለፍተሻ ከመኪና ውረዱ አሉን፡፡ 

ወርደን ለፍተሻ ዝግጁ ሆንን፡፡ መታወቂያቸው ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጋምቤላ፣ አፋር የሚል እንዲሳፈሩ ተፈቀደላቸው፡፡ አማራ የሚለውን 16 ሰዎች ሰብስበው እናንተ እንድታልፉ አይፈቀድም ብለው ሚዛን ተፈሪ ፖሊስ መምሪያ ወሰዱን፡፡ ከዚያም እስር ቤት አስገቡን፡፡ ከዚያም ሌላ 20 አማርኛ ተናጋሪዎች ተይዘው ታሰሩ፡፡ ምን አጠፋን? ወንጀል ሳንፈጽም ለምን ታስሩናላችሁ? ብለን ስንጠይቃቸው ወደዚያ ከሄዳችሁ አደጋ ይደርስባችኋል፡፡ ወደዚያ አማራ ሄዶ እንዲሰራ አይፈቀድም ብለውናል፡፡” ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡

“ትኬት ቆርጣችሁ ወደ አማራ ክልል ተመለሱ ብለው ከሦስት ቀን በኋላ የተወሰንን ሰዎችን ለቀቁን፡፡ ብዙዎቹ አሁንም በእስር ላይ ናቸው፡፡ እኛ ወደ ትውልድ መንደራችን ለመሄድ ገንዘባችንን ጨርሰናል፡፡ ብንሄድም ቦታ ስለሌለን ማረፊያ የለንም፡፡ ለዚህ ነው የቀን ሥራ ሠርተንም ጉርጓድ ቆፍረንም ህይወታችንን እንቀይራለን ብለን ጉዞ ጀምረን የነበረው፡፡ ሆኖም ግን አማራ በመሆናችን ተዘዋውረን ሠርተን እንዳንበላ ተደርገናል፡፡” ሲሉ አማረዋል፡፡

በመቀጠልም ሲናገሩ “እኛ ታስረን መፈታት ችለናል፡ ፡ ዛሬም ሥራ ፍለጋ ወደ ምንፈልግበት እንድንሄድና በነፃነት ከቦታ ቦታ እንድንቀሳቀስ አልተፈቀደልንም፡ ፡ ህጋዊን መንገድ ትተው በእግራቸው ጫካ ለጫካ ጉዞ የጀመሩ በርካታ ሰዎች ተገላዋል፡፡ በአውሬ ተበልተዋል፡፡ ሲገደሉም በአውሬ ሲበሉም የአካባቢው ኃላፊዎች ምንም የሚሰማቸው ፀፀት የለም፡፡ ህገ ወጦች ናቸው፡፡

እንኳን ሞቱ እንኳን ተበሉ እያሉ ሲሳለቁ ይሰማል፡፡” ካሉ በኋላ “የሚመለከተው የመንግስት አካል ጉዳዩን በጥሞና ተመልክቶ ውሳኔ ይሰጠን፡፡ ተዘዋውረን የመኖርና ሠርቶ የመብላት መብታችን እንዲከበርልን አሳውቁልን፡፡” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ የሚዛን ተፈሪ ፖሊስ መምሪያ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

Source: http://www.ethiomedia.com/2012_report/fenote_forty_four.pdf, ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ, PAGE 16

No comments:

Post a Comment