Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, December 6, 2012

ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ደብዳቤ ጻፉ

  •  “የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፤ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና ለሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ” ደብዳቤውን እንዲያውቁት የተባሉት መስሪያ ቤቶች
  •  ከስልጣኔ ውጪ ነው ያደረኩት ፤ በችኮላ የተጻፈ ደብዳቤ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ፤ በስሜትና በችኮላ የሆነ ነገር ነው ፤ ስለ ሰራሁት ስህተት አቡነ ናትናኤል ይቅርታ አድርጌልሃለሁ ብለውኛል” ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ
  •  “ይህ የእናንተ ጉዳይ አይደለም አያገባችሁም” አቃቢ መንበር አቡነ ናትናኤል
(አንድ አድርገን ህዳር 27 2005 ዓ.ም)፡-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አራተኛ ፓትርያርክ ብጹእ አቡነ መርቆርዮስ ከነሙሉ ክብራቸውና ማዕረጋቸው ወደቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱ የሚጋብዝ ከኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ደብዳቤ መጻፉ ተሰማ፡፡ 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች መካከል ቀኖና ተጣሰ በሚል ምክንያት በሁለቱ መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት በሰሜን አሜሪካው የሰላም ኮሚቴው አስተባባሪነት ሶስተኛውን የእርቀ ሰላም ድርድር ረቡዕ ህዳር 26 ቀን 2005 ዓ.ም በአሜሪካ ዳላስ ውስጥ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ለዚህው እርቀ ሰላም ጉባኤ ከአዲስ አበባው  ፩ኛ/ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የልዑካኑ መሪ፣ ፪ኛ/ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አባል፣ ፫ኛ/ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ አባል ፬ኛ/ ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ በጸሐፊነት  የተወከሉ ሲሆን ከአሜሪካው ሲኖዶስ ፩ኛ/ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የልዑካኑ መሪ፣ ፪ኛ/ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ አባል፣ ፫ኛ/ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አባል ፬ኛ/ ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ በጸሐፊነት ተወክለዋል፡፡  
የዳላሱ ጉባኤ ከመጀመሪያው የዋሽንግተን ጉባኤ ለየት የሚያደርገው አባቶች አብረው ጸልየውና አብረው ማዕድ ቀርበው የጀመሩት ጉባኤ በመሆኑ  ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል፡፡ “ውግዘት” የሚለው አልፈው አብረው በአንድ ማዕድ መቀመጣቸው እና አንድ ላይ ጸሎት ማድረጋቸው በዋነኛነት ሁለቱም ወገኖች ለሰላሙ መሳካት ፍላጎት እንዳላቸው ፤ ቀጥሎም የሰላምና የአንድነት ጉባኤውን ጥረት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ትላንት ህዳር 26  የተጀመረው የሰላም ጉባኤ አባቶች የሚነጋገሩበት ጉዳይ እና የሚደርሱበት የስምምነት ሃሳብ ምዕመኑ በከፍተኛ ተስፋ የሚጠብቀው ጉዳይ ሆኗል ፡፡ ይህ ደግሞ በዛሬ እና በነገ የሚታይ ውጤት ይሆናል፡፡

የኢ/ኦ/ተ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የእርቀ ሰላም ውይይት በሰሜን አሜሪካ ዳላስ ቴክሳስ
ይህ በእንዲህ እያለ ማክሰኞ ህዳር 25/03/2005 ዓ.ም በፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ስምና ፊርማ ከቤተመንግስት የሚቀጥለው ደብዳቤ መውጣቱ ታውቋል፡፡ 
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ባሉበት
ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ
የተጻፈው ደብዳቤ በአጭሩ…
ቅዱስነትዎ አራተኛው ፓትርያርክ ሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መሾሞ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በተከሰተው ሁኔታ ምክንያት ቅዱስነትዎ ከሀገር መውጣት ምክንያት እና በምትኩም ፓትርያርክ ተሹሞ መቆየቱ ግልጽ ሆኖ ሳለ  በምትኩ የተሾሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል ፡፡  ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ህልፈተ ህይወት ቀጥሎ ስለ ፓትርያርክ መሾም በተመለከተ ጉዳዩ ተነስቶ የሀገር ሽማግሌዎችና የእምነት ተከታዮች “ለቤተክርስቲያኒቱ አንድነት ሲባል ሌላ ፓትርያርክ መሾም የለበትም ፤ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው ከሙሉ ክብራቸውጋር መመለስ አለባቸው ፡፡ ተከፋፍሎ የነበረውም ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ አንድነት መምጣት አለበት” ተብሎ በቀረበው የሀገር ውስጥ ሽማግሌዎች ሀሳብ መሰረት እኛ ሀሳቡን ሙሉ ለሙሉ ተቀብለነዋል ፡፡  ቅዱስነትዎ ይህን ሃሳብ ተቀብለው ልዩነቱን በማጥበብ በቤተክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም እንዲሰፍን በቅዱስነትዎ የሚመራውን ቅዱስ ሲኖዶስ ይዘው ወደ ሀገርዎ እና ወደ ቤተክርስቲያንዎ እንዲገቡ ይህን ደብዳቤ ጽፈናል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ፕሬዝዳትን ግርማ ወ/ጊዮርጊስ
የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት
ፊርማ እና ማህተብ
እንዲያውቁት
  • ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ
  •  ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
  •  ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር
  •  ለሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር
ግልባጭ
  •     ለኢንጂነር አራጋው ጥሩነህ የሚመራው የሽማግሌዎች ቡድን
        አዲስ አበባ
የአርበኛ አባቶች ማህበር መሪ ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ እና ኢንጂነር አራጋው ጥሩነህ እና ሌሎች የሽማግሌ ቡድን የሚመራው አካል ፕሬዝዳንቱ ጋር በመቅረብ የቀድሞ ፓትርያርክ በአቶ ታምራት ላይኔ ሴራ አማካኝነት ከሀገር እንደተሰደዱ እና በአሁኑ ሰዓት ቤተክርስቲያኒቱ በሁለት ሲኖዶስ እንደምትመራ በመወያየት ይህም አግባብ አለመሆኑን በመናገር ይህን ደብዳቤ ከፕሬዝዳንቱ ስልጣን ውጪ እንዲጻፍ አድርገዋል፡፡ ክቡር ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ለቪኦኤ የአማርኛው ድምጽ በመጀመሪያ ደብዳቤው ከእሳቸው ቢሮ በእሳቸው ማህተብ እንደወጣ እና በኋላ ግን የተሰጣቸው ስልጣን ይህን ለማድረግ እንደማይፈቅድላቸው ሲገነዘቡት እንደገና ደብዳቤው ከተበተነበት እንዲሰበሰብ እንዳደረጉ ተናግረዋል ፡፡
ከፕሬዝዳንት ግርማ አንደበት
“ያ ደብዳቤ ስህተት ሆኖ ስለተገኝ እንዲመለስ ብለናል ፤ የሆነ ሆኖ ይህ የመንግስት ትዕዛዝ አይደለም የግለሰብ ሀሳብ ነው ፤ በእኔ በኩል Contradict አድርጌዋለሁ ፤ ከስልጣኔ ውጪ ነው ያደረኩት ፤ በችኮላ የተሰራ ስራ ስለሆነ ትቼዋለሁ ፤ በስሜትና በችኮላ የሆነ ነገር ነው ፤ በሰዎች ሀሳብ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ደብዳቤ ነው ፤ ሌላ ችግር እንደሚያመጣ አላገናዘብኩኝም    በመጀመሪያ አቡነ ናትናኤል ናቸው የተቃወሙት ፤ አቡነ ናትናኤል “ይህ የእናንተ ጉዳይ አይደለም አያገባችሁም” አሉን ፤ አቡነ ናትናኤልን በስልክ አግኝቻቸው ነበር እና “ይቅርታ አድርጌልሀለሁ” ብለውኛል” በማለት ለቪኦኤ ጋዜጠኛ ለአቶ አዲስ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡
የአንድ አድርገን ሃሳብ
እስከ አሁን ያሳለፍነው ጊዜ ማብቂያው በተቃረበበት ወቅት የምንሰጣቸውን አስተያየቶች የምንጽፋቸውን ሃሳቦች እርቀ ሰላሙ ላይ የሚያመጣውን እንቅፋት እንዳይኖር ልንጠነቀቅ ይገባል ፡፡ ይህ እርቀ ሰላም እንዲሳካ የሚፈልጉ በርካታ ምዕመናን እንዳሉ ሁሉ እኛን ከማይመስሉ ከወዲያ ግድም የቆሙ እርቀ ሰላሙ ቢፈጸም ጥቅማቸውን የሚነካባቸው ሰዎች እርቀ ሰላሙ በሰላም እንዳያልቅ የበኩላቸውን የማሰናከያ ጥረት እንደሚያደርጉ ልንዘነጋ አይገባም ፡፡  ከሽማግሌ ነን ባዮች ጀርባ ማን እንዳለም ለመገመት ያስቸግራል ፤ ለህዝበ ክርስቲያንና ለቤተክርስቲያን በማይጠቅም አካሄድ ፓትርያርክ ለማስቀመጥም ውስጥ ውስጡን የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉም እናውቃለን ፡፡ በማወቅም ሆነ  ባለማወቅ የሚደረጉ እንቅፋቶችን ቀድመን ልንከላከል ያስፈልጋል ፡፡ 
አሁን ይህ ደብዳቤ ከቤተመንግስቱ ራሳቸውን የሽማግሌዎች የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ ብለው በመሰየም ትልቅ እይታ ለማግኝት በፕሬዝዳንቱ በኩል ደብዳቤ ሲያጽፉ በመጀመሪያ የተቃወሙት እና “እናንተ ይህ ጉዳይ አያገባችሁም” ብለው ቀጥተኛ ምላሽ የሰጡት አቃቢ መንበር አቡነ ናትናኤል መሆናቸው ደስ ያሰኛል፡፡ በአሁን ሰዓት ቤተክርስቲያን ስለ ውጫዊ ተፅህኖ በፊት ለፊት የሚጋፈጥ አባት ያስፈልጋታል፡፡ በጉዳዩ የማያገባውን አካል በግልጽ “አያገባህም” ተብሎ ሊነገረው ይገባል፡፡  የዛሬ 20 ዓመት መንግሥት ያን ሁሉ ሴራ ቤተክርስቲያን ላይ ሲዶልት እና ሲሰራ እንደ አቡነ ናትናኤል “አያገባህም” ብሎ የሚናገረው አባት በግልጽ ቢኖር ኖሮ እኛም 20 የችግር ፤ የጎጠኝነት ፤ የዘረኝነት ፤ ያለመግባባት ፤ የመከፋፋል ፤ የሁለት ፓትርያርክና  የሁለት ሲኖዶስ ጊዜ ባላሳለፍን ነበር፡፡ ጊዜ ቢወስድም አንድ መሆናችን እንደማይቀር እናምናለን ፤ አሁንም ቢሆን አባቶች ይህን እግዚአብሔር ቤተክርስቲያኒቱ አንድ እንርትሆን ያመጣውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መንግሥት በማንኛውም ሰዓት ስለ ቤተክርስቲያን ፤ ስለ ቀጣይ ፓትርያርክ እና መሰል የማያገባው ጉዳይ ላይ ገብቼ አስታራቂ ሃሳብ ልስጥ ቢል ሲኖዶሱ በአንድ ድምጽ እንደ አቃቢ መንበር አቡነ ናትናኤል “አያገባህም” ብለው መናገር መቻል አለባቸው ፡፡
አቃቢ መንበሩ እንደ አንድ የሃይማኖት አባት ከፕሬዝዳንት ግርማ ጋር ስለተጻፈው ደብዳቤ በመወያየት ያደረጉላቸው ይቅርታ እጅጉን ደስ የሚያሰኝ ነገር ሆኖ አግኝተነዋል ፡፡ ፕሬዝዳንቱም የሰሩት ስራ አግባብ አለመሆኑን ተረድተው ስህተታቸውን አሜን ብለው መቀበላቸውም ጥሩ ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ግርማ ቀኝ ግራውን ባለማስተዋል የ20 ዓመቱን ታሪክ ወደ ኋላ ሄዶ ባለመቃኝት  በሰዎች ገፋፊነት የ20 ዓመትን ክፍተት በትንሽ ደቂቃ ንግግር ለመፍታት የጻፉት ደብዳቤ  እርቁ ላይ ሌላ ጥላ ሳያጠላ በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ ማድረጋቸው  መልካም ነው ፡፡ ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ይህ የአንድ ሰው ሃሳብ እንጂ የመንግሥት አለመሆኑን ተናግረዋል ፤ መንግሥትም ለሕገ-መንግሥቱ ተግባራዊነት በተጀመረው እርቀ ሰላም ዙሪያ እጁን ባያስገባ ለህዝብ ፤ ለቤተክርስቲያን ፤ ለሀገርና ለመጪው ትውልድ ፍጹም ሰላም ጥሩ ነው የሚል አስተያየት አለን፡፡

በአሜሪካ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የተጀመረውን እርቀ ሰላም ጫፍ ያደርስልን ዘንድ የእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ይሁንልን፡፡
       
           
    
                  
                                
                      
 
 

No comments:

Post a Comment