Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, August 23, 2012

ስለ አቶ መለስን ሞት የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አስተያየት

ኢሳት ዜና:-  ነሀሴ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
“በኢትዮጵያ የመሪነት ሥልጣን የሚይዘው ሰው የሚመራበትን ሁኔታ ራሱ መምረጥ ይኖርበታል፡፡ የሚመራበትን ሁኔታ በፓርቲ ማዕቀፍ ውስጥ አስገብቶ መስጠት የሚመራውን ሰው መናቅ ነው ብዬ ነው የማስበው” ሲሉ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ተናገሩ።

በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ  በጠቅላይ ሚኒስትር  መለስ ሞት ሀዘን እንደተሰማቸው በመግለፅ፦” ፤”ከእንግዲህ በሞተ ሰው ላይ እንዲህ ነው- እንዲያ ነው ማለት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሳይሞቱ ቢሆን ኖሮ ብዙ ነገር መማማር ይቻል ነበር፡፡ በሕይወት እያሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፦ አምባገነን፣ ጨካኝ፣ ወዘተ በማለት ብዙ ኃይለ ቃል ተጠቅመን ገልጸናቸው ይሆናል፡፡ አሁን በሞተ ሰው ላይ ምንም ማለት አስፈላጊም አይደለም”ብለዋል።


“ ከዚህ በኋላ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለው ነገር ፤ታሪክ የሚሆንና ታሪክ የሚፈርደው ጉዳይ ነው”ያሉት በፓርላማ   የአንድነት ፓርቲው ተወካይ፤  ከአሁን በኋላ  የምንናገረው ነገር፤ ፓርቲያቸው የሚወስዳቸውን አቋሞች በማየት የምንለው ነገር ይሆናል” በማለት  በአሁኑ ጊዜ በኢህአዴግ እየታዬ ነው ያሉትን ስህተት ተናግረዋል።

እንደ አቶ ግርማ ገለፃ፤ በአሁኑ ጊዜ የ ኢህአዴግ ሹማምንት የሚሰጧቸው መግለጫዎችና ንግግሮች  ፓርቲውን የሚያስገምቱ ናቸው።

ከነዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው፦ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተሳሰብ፣ እይታና ሌሎች ነገሮችን ይዘን እንቀጥላለን›› የሚባለው ነገር እንደሆነ አቶ ግርማ አመልክተዋል።

አቶ መለስ በህይወት ዘመናቸው የበላይነት እንደነበራቸው ቢታወቅም፤ ‹‹ ይህ አባባል ፓርቲው የአንድ ሰው ነበር?›› የሚለውን ጥያቄ በማስነሳት – ኢሕአዴግን እንደ ገዥ ፓርቲ እንደሚያስገምተው አቶ ግርማ አስረድተዋል።

“መሪ ሆኖ የሚመጣው ሰው የራሱን እይታ ይዞ የሚመራበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ለምሳሌ የእኔን መኪና እኔ ስነዳውና አንተ ስትነዳው ይለያያል፡፡የሚለያየው፤ እስከምትለማመደው ብቻ አይደለም፡፡ የአነዳድ ሁኔታው ሁሉ ነው የሚለያየው፡፡ ስለዚህ ለሚቀጥለው መሪ መብት ስትሰጠው ‹‹በፈለግኩት አቅጣጫ ነው የምትመራኝ›› ካልከው ፤የፓርቲውን ደረጃ ያወርደዋል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

አቶ ግርማ አያይዘውም፦”የመሪነት ሥልጣን የሚይዘው ሰው የሚመራበትን ሁኔታ ራሱ መምረጥ ይኖርበታል፡፡ የሚመራበትን ሁኔታ በፓርቲ ማዕቀፍ ውስጥ አስገብቶ መስጠት፤ የሚመራውን ሰው መናቅ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላሉ አይደለም በሰላምና በፍቅር የሚኖሩት፡፡ አሁንም በሰላም መኖራቸው ይቀጥላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ታመዋልና ምን እንሆናለን?›› ሲሉ፤ ምንም አንሆንም ነው ያልነው፡፡ አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም አይሆንም፡፡ ግን ደግሞ ምንም የማይሆኑ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥላ ጠብቀው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ካሉ፤ ቢፈሩና ቢሰጉ ተገቢ ነው፡፡ የሚያስፈራቸውና የሚያሰጋቸው የሠሩት ሥራ እንጂ ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም፡፡ መልካም እንቅልፍ ለመተኛት ጥሩ ሥራ መሥራት አለብህ፡፡”ብለዋል።

እንደ ሪፖርተር ዘገባ፤ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሞታቸውን ሢሰሙ ከልብ ማዘናቸውን የገለጹት ሌላው የአንደነት አመራር አቶ ተመስገን ዘውዴ በበኩላቸው፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ብዙ ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው ብዙዎችን ሀሳቦች በራሳቸው አስተሣሰብ ለመግለጽና  ለማሳመን አቅም እንዳላቸው፤  ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሥር እንዲሰድና አቅም እንዲኖረው፣ እንዲሁም ታማኝነት ያለው የፖለቲካ አቅጣጫ እንዲፈጠርና የተለያየ አመለካከት ያላቸው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ የነበራቸው አስተዋጽኦ ደካማ እንደ ነበር አውስተዋል።

በመሆኑም  ቀጣዩ የኢሕአዴግ አመራር ለሕዝብ ታማኝነት ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማሰባሰብ፣ እኛም ተቃዋሚዎች አገራችን  ነፃነቷን፣ ክብሯንና ህልውናዋን ጠብቃ በሰላም ወደፊት እንድትራመድ አስተዋጽኦ እንዲኖረን፣  የፖለቲካ መድረኩን ማስፋት አለበት”ሲሉ አሣስበዋል።

“እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት አሳዝኖኛል፡፡”ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት፤ወደፊትም የሰከነና የረጋ አመራር እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች የተከፋ ሰው ሊኖር ስለሚችልና ሐዘንም ሲጨመር ከባድ ነገር ሊሆን ስለሚችል፣ አስተዋይነትና አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡”ሲሉ መክረዋል።

“እኔ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገራችን ባህል ሰው እንዲህ ዓይነት ነገር ሲገጥመው ነፍሱን ይማረው እላለሁ፡፡ “በማለት አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩት የ ኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ አመራር ዶክተር መረራ ጉዲና  በበኩላቸው፦”የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ስሰማ ደንግጫለሁ።  ነገር ግን አገሪቷ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመፍጠር ረገድ  እጅግ አጣብቂኝ የሆነ ነገር ውስጥ ስለገባች፣ የተሻለች ኢትዮጵያን በጋራ ለመፍጠርና ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲኖር፤ አጋጣሚውን እንዲጠቀምበት ገዥውን ፓርቲ አደራ እላለሁ፡፡”ብለዋል።

ሌለኛው የ አንድነት አመራር አቶ ስዬ አብርሀ  በበኩላቸው  ከአውራምባ ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በቀድሞ ጓዳቸው ሞት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ጠቅሰው፤ በአገሪቷ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ እንዲኖር ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች የየበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉና የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዳኛ  ብርቱካን ሚዴቅሳ በበኩሏ በአቶ መለስ ሞት ሀዘን እንደተሰማት በመግለጽ፤  ቀሪው የ ኢህአዴግ አመራር ሁሉን አቀፍ ሥርዓት በመፍጠር በኩል ብዙ እንደሚጠበቅበት አሣስባለች።ባለፉት ጊዜያት የደረሱ ጉዳቶች የሚረሱት፤ ፍትህ የሰፈነባትና የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያ ስትገነባ ብቻ እንደሆነ በማስረገጥ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት በበኩሉ ፦”ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት በ አስቸኳይ ይቋቋም!”በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ግን፦”ኢትዮጵያ ባሁኑ ወቅት የሚያስፈልጋት ስር ነቀል ለዉጥ እንጂ አበዉ “ጉልቻ ቢለዋወጥ ..” እንደሚሉት የስልጣን ሽግሽግአይደለም። አዉነተኛ ሀገር አፍቃሪ ነን ለምንል ወገኖችም ጊዜዉና አጋጣሚዉ እጅግ አመቺ ሆኗል። ከዚህ አንጻርሉአላዊነቷና አንድነቷ የተጠበቀ፤ ፍትሃዊና፤ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመገንባት ሁሉን አቀፍ የሆነና ባለድርሻ አካላትን ያካተተየሽግግር መንግስት በአስቸኳይ ዛሬ ነገ ሳይባል እንዲቋቋም ጥሪያችንን እናቀርባለን!”ብሏል።

ይሁንና ገዥው ፓርቲ ሥርዓቱ ምንም ዓይነት የፖሊሲ ለውጥ ሳያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀደዱት መስመር እንደሚሄድ ነው በተደጋጋሚ እየገለጸ ያለው። ግንቦት 7 ለፍትህ፣ለነፃነት እና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ በበኩሉ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀመረውን የነፃነት፣ የመብትና የክብር ትግል አጠናክሮ  እንዲገፋበት ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ለሲቪክ ማህበራት እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ አቅርቧል።

“የኢትዮጵያ ህዝብ በመለስ ዜናዊ ሞት ዙሪያ፤ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገራት ጥቅም ተካፋዮቹ የሚሰሩትን ትዕይንት በማየትና በመስማት የሚያጠፋው ግዜ አይኖርም” ያለው ግንቦት 7፤ የሕዝቡ ትኩረትና ጥድፊያ መለስ ዜናዊ ጥሎት በሄደው አፋኝ ሥርዓት መቃብር ላይ – ዝንተ ዓለም ሲመኘው የኖረውን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት፤ ከነፃነትና ከሰብአዊ ክብር ጋር የተሳሰረ ብልጽግና እና የህግ የበላይነት የሰፈነበት ሃገር መገንባት ነው።”ብሏል።

በሌላ በኩል አቶ መለስን ተክተው በተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲሠሩ ኃላፊነት የተጣለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ትናንት ምሽት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሰጡት መግለጫ፦  አቶ መለስን መተካት እንደሚከብዳቸው ተናግረዋል፦‹‹መለስን መተካት ከባድ ነው›› በማለት።

No comments:

Post a Comment