Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, July 18, 2012

የሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ታሰሩ

ኢሳት ዜና:- ሐምሌ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ የ አቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ከሳዑዲ ዓረቢያ የሃይማኖት አታሼ ቢሮ ገንዘብ ይዘው ሲወጡ ተይዘው መታሰራቸውን ሰንደቅ ጋዜጣ ዘገበ።

ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሐመድ መሐሙድ ፤በወረዳ 17 ወርቁ ሕንፃ አጠገብ ከሚገኘው ከሳዑዲ ዓረቢያ የሃይማኖት አታሼ ቢሮ ግምቱ ከሃምሳ እስከ መቶ ሺ ብር የሚገመት የታሰረ ገንዘብ እና በዓረብኛ የተፃፉ መፅሐፍት ይዘው ሲወጡ በፌዴራል ፖሊስ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።


ወይዘሮ ሃቢባ መሐመድ  እጅ ከፍን ጅ ተይዘው  በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ ትናንት ሐምሌ 10 ቀን 2004 ዓ.ም በሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ውስጥ የሃይማኖት አታሼ ኃላፊ ከሆኑት ፋህድል ቃህታኒ ቢሮ ውስጥ ከቀኑ ከ8፡30 እስከ 9፡30 ሰዓት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ቆይታ አድርገው ሲወጡ  ነው።

ወይዘሮ ሃቢባ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያው የሃይማኖት አታሼ ቅጥር ግቢ ውስጥ የገቡትም፤የሰሌዳ ቁጥሩ 65602 በሆነ  የመንግስት ነጭ ኮብራ መኪና  ሲሆን፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፖሊስ በዚሁ ላንድክሩዘር መኪና ውስጥ ባካሄደው ፍተሻ በአራት ካርቶን ውስጥ በቁጥር አምስት መቶ የሚሆኑ በዓረብኛ ቋንቋ የተፃፉ መፃሐፍት ተገኝተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የማብሰያ መሣሪያዎች ከላንድክሩዘሩ መቀመጫ በስተጀርባ ላይ ተጭነው መገኘታቸውን የጋዜጣው ምንጮች ተናግረዋል። ወይዘሮ ሃቢባ ወደ ሳዑዲው የሀይማኖት አታሼ ቢሮ ሲገቡ፤ አንድ የአቶ ጁነዲን ሳዶ የግል ጠባቂና ሹፌራቸው አብሯቸው እንደነበሩ ምንጮቹ ጨምረው ጠቁመዋል።

ጋዜጣው፦“ ወይዘሮ ሀቢባ የተያዙት የመንግስት ንብረት በሆነ ተሽከርካሪ ወደ ሚስተር ፋህድል ቢሮ ስለገቡ ነው? ወይንስ ከኤምባሲው የሃይማኖት አታሼ ኃላፊ  ጋር  የተለየ ግንኙነት ፈጥረዋል በሚል ነው? ወይንስ የተለየ ተልዕኮ ሊኖራቸው ይችላል ከሚል ስጋት ነው?” በማለት ጥያቄ ያቀረበላቸው አንድ የማዕከላዊ ፖሊስ ሀላፊ፤  የወይዘሮ ሃቢባ መሐመድን መታሰር አምነው፤ ሆኖም ግን ጉዳዩ በምርመራ ላይ ያለ በመሆኑ ዝርዝር መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment