Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, April 29, 2012

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል በሚል የወጣውን መረጃ ተከትሎ ኤርትራ ውጥረት ውስጥ ገብታለች

 ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል በሚል የወጣውን መረጃ ተከትሎ ኤርትራ ውጥረት ውስጥ ገብታለች፡፡ አስመራን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ከፍተኛ የሚሊተሪ እንቅስቃሴ መኖሩን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ላለፈው አንድ ወር ያህል ከሚዲያ የራቁት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከዚህ ዓለም በሞት ስለመለየታቸው በእርግጠኝነት የሚናገሩ የመኖራቸውን ያህል፣ አልሞቱም ግን ኮማ ውስጥ ገብተዋል የሚሉ ወገኖችም አልጠፉም፡፡

የኤርትራ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በበኩሉ አቶ ኢሳያስ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ‹‹ፕሬዚዳንቱ ሞተዋል›› የሚለውን የተሳሳተ መረጃ የሚያናፍሱትም ሲአይኤና ኢትዮጵያ መሆናቸውን እየገለጸ ይገኛል፡፡ በቴሌቪዥን የሚታየው የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ምስል ግን ከወራት በፊት የተቀረጸ መሆኑን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ መሞታቸው በሚነገርበት በአሁኑ ጊዜ አስመራ ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚታይ ሲሆን፣ አገሪቱን ማን ነው እየመራት ያለው የሚለው ጉዳይ ግን በግልጽ ሊታወቅ አልቻለም፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሞተዋል የሚል እምነት ያላቸው አንዳንድ ተንታኞች የፕሬዚዳንቱ ዜና ዕረፍት ይፋ ያልሆነው ተተኪ እስከሚዘጋጅ ድረስ ግርግር እንዳይፈጠር ታስቦ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ሌሎች ወገኖች በበኩላቸው አቶ ኢሳያስ ኮማ ውስጥ ገብተው መሥራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሞተዋል ተብሎ በስፋት እየተወራ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አሊ አብዱ፣ ‹‹ኢሳያስ አፈወርቂ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል›› ብለዋል፡፡ 

ከአንድ ሳምንት በፊት ጀምሮ መነጋገሪያ የሆነውን ይህንን ጉዳይ የሚያናፍሱት ቡድኖች ኤርትራን ለማተራመስ ምኞት ያላቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ ሁልጊዜ አገኘዋለሁ፤ ዛሬ ጠዋት [ትናንት] 3፡00 ላይ አይቼዋለሁ፤ ኢሳያስ አፈወርቂ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል፤ ይህንን በጉልህ ፊደላት ልትጽፈው ትችላለህ፤›› ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለሚወራባቸው ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ምላሽ ለመስጠት ሲባል በቴሌቪዥን የሚታዩበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ አቶ ኢሳያስ ሞተዋል ወይም ኮማ ውስጥ ናቸው በመባሉ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ኤርትራን ማን እየመራት ነው የሚለው ኤርትራውያንን ግራ እንዳጋባቸው ይነገራል፡፡ ሞተዋል ተብሎ ግርግር እንዳይነሳ ነው እንጂ ሰውዬው ሳያበቃላቸው አይቀርም የሚሉም አሉ፡፡ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ደጋፊዎች ሠራዊቱን ይዘው የበላይነት ይዘዋል የሚሉ ሲኖሩ፣ ይህንን የሚቃወሙ ደግሞ ውስጥ ለውስጥ የሚቃወሙዋቸው ዝግጅታቸውን ጨርሰው ሥልጣን ሳይቀሙ አይቀሩም ይላሉ፡፡

 በአስመራ ከተማ ውስጥ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች መታየት ከጀመሩ ወዲህ ሁለት ያሸመቁ ጎራዎች ሳይኖሩ እንደማይቀሩ በስፋት ይወራል፡፡ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም በትናንትናው ዕለት የኢሳያስን ወቅታዊ ሁኔታ ከምንጩ ለማግኘት ሲቸገሩ ታይተዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እየተነጠለ የመጣው የኢሳያስ መንግሥት ከዓረቦች አብዮት በኋላ ከተለያዩ አገሮች ያገኘው የነበረው ድጋፍ ተቋርጦበታል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የነበሩት ሆስኒ ሙባረክና ሙአመር ጋዳፊ በሕዝባዊ አመፅ ከሥልጣን መወገዳቸው የኤርትራ ካርዶች እየረገፉ መምጣታቸውን እንደሚያመላክት እነኚሁ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

ምንጭ ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment