Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, April 6, 2012

አባቶችና ልጆች

ወደ ጎንደር የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ለማስተማር የመጣ አንድ ጀርመናዊ ሃኪም አንዲት የገበሬ ሚስት እያከመ ነበር። እንዴት ሾልኮ እንደገባ ባይታወቅም የሴትየዋ ባል ከሚስቱ ራስጌ ላይ ቆሟል። ገበሬው የታመመች ሚስቱን በስስት አይን፣ ፈረንጁን ሃኪም ደግሞ በተስፋ ይመለከታል። ጀርመናዊው ሃኪም ቆጣ ብሎ ከሚስቱ ራስጌ ተጠግቶ የቆመውን ገበሬ እንዲያስወጡት አዘዘ። ረዳቶቹ ገበሬውን እየገፈታተሩ አስወጡት። ፈረንጁም ህክምናውን ጀመረ…
* * *
በግምት ከሶስት ሰአታት በሁዋላ የሰላ ጎራዴ የያዘ አንድ ገበሬ የጎንደር ሆስፒታልን ቀውጢ አደረገው። የሆስፒታሉ ሪሴፕሽን ላይ ጎራዴውን እያወናጨፈ፣ እንደ ጥይት በሚተኮስ ድምፅ ይጮህ ጀመር፣
“አምጡልኝ፣ ያንን ነጫጭባ ጣልያን! እንደ ገበሎ ወገቡን ሁለት ቦታ ላይ ካልቀነጠስኩት እኔ የአባቴ ልጅ አይደለሁም!”
ሆስፒታሉ በዚያው ቅፅበት ተተራመሰ!
ሁኔታው ወዴት እንደሚያመራ የገባቸው ነባር ሃኪሞችና ነርሶች ጀርመናዊውን ሃኪም ቢሮ ውስጥ ቆልፈውበት በውጭና በውስጥ ፈረንጁን ከበውት ለጥበቃ ቆሙ። አንዲት ነርስ ወደ ጎንደር ፖሊስ በመደወል አስቸኳይ የእርዳታ ጥሪ አደረገች። የሆስፒታሉ የጥበቃ ዘቦች አእምሮውን የሳተ የሚመስለውን ባለጎራዴ በርቀት ከብበው ይማፀኑት ጀመር፣
“እባክህ ረጋ በል!”
ገበሬው ግን ሊረጋጋ አልቻለም።
“ገለል በሉ ከፊቴ! ሁዋላ ሰበብ ትሆናላችሁ! ከእናንተ ጠብ የለኝም! ገለል በሉ ብያለሁ…”
“እባክህ ረጋ በል ጌታው! ጎራዴውን አስቀምጥና እንነጋገር!?”
“በህግ አምላክ ሰበብ አትሁኑብኝ!”
ገበሬው ጎራዴውን ልክ እንደ ገብስ አጨዳ አይነት፣ አየሩ ላይ እየሰነዘረ፣ አየሩን በሰላ ጎራዴው ያጭደዋል። እንደሚገነፍል የጀበና ቡና ያለ የእልህ ቁጣ ከልቡ ብልቃጥ እየተተኮሰ፣ እንደ ማቅራራት ያደርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጀርመናዊው ሃኪም እጅና እግሩ እየተንቀጠቀጠ ወደ ጀርመን ኤምባሲ ለመደወል ቢጠይቅም፣ እጁን ይዘው እንደምንም አረጋጉት። ባለ ጎራዴው ገበሬ ዘቦቹን ጥሶ ቢመጣ እንኳ፣ የሆስፒታሉን ሃኪሞችና ነርሶች ገድሎ ሳይጨርስ እሱ ዘንድ ሊደርስ እንደማይችል በእርግጠኛነት ቃላቸውን ሰጡት።
በዚህ መካከል ፖሊሶች ደረሱ። እነርሱም እንደ ዘቦቹ፣ ጠመንጃቸውን አቀባብለው ገበሬው ላይ በመደገን ጎራዴውን እንዲያስቀምጥ መማፀን ጀመሩ። ግማሽ ሰአት እንኳ ባልወሰደው በዚህ ቅፅበታዊ ግርግር ውስጥ፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ነባር የሆነ አንድ የአስተዳደር ሰራተኛ መፍትሄ አበጀ። በሆስፒታሉ ውስጥ ለህክምና ከተኙ ከበድ ያሉ አዛውንቶች መካከል ሁለቱን መርጦ በማምጣት፣ ወደ ባለጎራዴው ተጠግተው እንዲያነጋግሩት ፖለሶቹም ገለል እንዲሉ አደረገ።
ከአስር ደቂቃ በሁዋላ ባለጎራዴው ረገብ አለ። ጎራዴውን ማወዛወዙንም ቀነሰ። በመቀጠል ስለተፈጠረው ችግር ለጀርመናዊው ሃኪም ገለፃ ተደረገለት። ገበሬው ለምን ሊገድለው እንደመጣ ለጀርመናዊው ማብራሪያ ሲደረግለት፣ በድንጋጤ ደሙ ከፊቱ ላይ ጥርግርግ ብሎ ጠፍቶ፣ ያልተፃፈበት ነጭ ወረቀት መስሎ እንደነበር አጠገቡ የነበሩት መስክረዋል። ሆኖም ችግሩ ሊወገድ እንደሚችል በእርግጠኛነት ነገሩት። በርግጥ ገበሬውን በቁጥጥር ስር ማድረግ እንደሚቻል ነግረውታል። መፍትሄ እንደማይሆን ግን አስረዱት። የገበሬው ዘመዶች ሊበቀሉት እንደሚችሉ በመጠቆም፣ የሚሻለው እርቅ መሆኑን ጠቆሙት።  ጀርመናዊው ሃኪም ምን ጥፋት እንደፈፀመ በትክክል ሊገባው ባይችልም የተፈጠረውን ከፍተኛ ግርገር በመመልከት አንድ አደገኛ ነገር መከሰቱን ተገንዝቦ ስለነበር፣ ምንም ሳያመነታ ገበሬውን ይቅርታ ለመጠየቅ ተስማማ፣
* * *
እነሆ! ገበሬውና ሃኪሙ በሰዎች እንደታጀቡ በየተራ የገበሬው ሚስት ወደተኛችበት የበሽተኛ ክፍል እንዲገቡ ተደረገ። ገበሬው ጎራዴውን እንደጨበጠ ከሚስቱ ራስጌ አጠገብ ቆመ። ጀርመናዊው ሃኪም ከበሽተኛዋ አልጋ ግርጌ በኩል እንዲቆም አደረጉት። አሸማጋዮቹና የሆስፒታሉ ጥቂት ዶክተሮች በመካከል ላይ ቆሙ። በአገሩ ባህል መሰረትም አሸማጋዮቹ የተፈጠረውን ችግር በዝርዝር አብራሩ። ከዚያም በአስተርጓሚ በኩል ፈረንጁን እንዲህ አሉት፣
“የህመምተኛዋን የተከበሩ ባል በማመናጨቅ መልኩ እጅህን አወዛውዘህ፣ ‘አስወጡት!’ ማለትህ ልክ አይደለም። እሳቸው ባለቤታቸው እንደመሆናቸው ከዚህ መውጣት ካለባቸውም በጨዋ ደንብ ለብቻቸው ገለል በማድረግ ሊነገራቸው ይገባል እንጂ፣ ሚስታቸው ፊት በዚህ መንገድ ማመናጨቁ ክብር የሚነካ ነው። እሳቸውም እንዲህ ሚስታቸው ፊት ክብራቸው ተነክቶ፣ አባወራ ሆነው መኖር ስለማይችሉ ጎራዴያቸውን ይዘው መጥተዋል። ርግጥ ነው፣ እርስዎም እንግዳችን እንደመሆንዎ መከበር አለቦት። እንዲህ ያለ ነገር በመፈጠሩም አዝነናል። የእግዚአብሄር ፀጋ አልተለየንምና ግን በመካከላችሁ ደም አልፈሰሰም። አሁን እርስዎም በደል እንደፈፀሙባቸው አውቀው፣ በሚስታቸው ፊት ይቅርታ ይጠይቋቸው!”
ጀርመናዊው ሃኪም በሽማግሌዎቹ በተመከረው መሰረት በአስተርጓሚ ምላሽ ሰጠ፣
“በእውነቱ እሳቸው የህመምተኛዋ ባል መሆናቸውን አላወቅሁም ነበር። የአነጋገር ጠባይና ልማድ ሆኖብኝ እንጂ ማመናጨቄም አልነበረም። ከሃገሬ ድረስ ሌሊትና ቀን ተጉዤ እዚህ መምጣቴ የታመሙትን ለመርዳት እንጂ ክብር ለመንካት አይደለም። መቼም አጥፍቼ ከሆነ እሳቸውንም ባለቤታቸውንም ይቅርታ እጠይቃለሁ!”
ሃኪሙ የተናገረው ለገበሬውና ለሚስቱ ተተርጉሞ ሲነገራቸው፣ ሁለቱም ስሜታዊ ሆነው በነጠላቸው ጫፍ አይኖቻቸውን አባብሰዋል። ገበሬውም በዚያችው ቅፅበት ጎራዴውን ከሽማግሎቹ ለአንዱ ካስረከበ በሁዋላ፣ የሚከተለውን ተናገረ፣
“እኔም ብሆን ሚስቴን ከህመሟ ይፈውሱልኛል ብዬ ተስፋ ያደረግሁት በርስዎ ላይ ነው። የክብር ነገር ሆነብኝና ግን አስቀየምሁዎ! ጣሊያን መስለውኝ ያለ ስምዎ ስም በመስጠቴና በመዝለፌ እኔም ብሆን ይቅርታ እጠይቃለሁ። ሊያጠቃኝ ጎራዴ መዘዘብኝ ብለው በልብዎ ቂም ይዘው ሚስቴን ችላ እንዳይሉብኝም ርስዎም ቃሎን ይስጡኝ”
ይህ የገበሬው ንግግር ለፈረንጁ ሃኪም ሲተረጎምለት ፊቱ የማረቆ ድልህ መምሰሉ ታይቶአል። ሚስትየዋ አንዳችም ያልተናገረች ሲሆን፣ ፈረንጁ ይቅርታ ሲጠይቅ ግን ከወገቧ እንደመነሳት ብላ፣ “አይገባም” እንደማለት አክብሮቷን ገልፃለታለች። በዚህ መልኩ እርቁ ከተፈፀመ በሁዋላ ሁለቱ በእድሜ የሚቀራረቡ ባላንጣዎች ትከሻ ለትከሻ እንዲሳሳሙ አደረጓቸው።
* * *
ይህን ታሪክ ያጫወተኝ በወቅቱ ከኮሌጁ የህክምና ተማሪዎች አንዱ የነበረ ጓደኛዬ ሲሆን፣ ታሪኩ ከተፈፀመም 19 አመታት ሆኖታል። ሆኖም ይህ ታሪክ አእምሮዬ ላይ ነግሶ እንደመኖሩ፣ የክብር ጉዳይ በተነሳ ቁጥር በጨዋታ መሃል ስጠቅሰው ኖሬያለሁ። ርግጥ ነው፣ ያ የበጌምድር ገበሬ ከኛ ዘመን ትውልድ ጋር የመንፈስ ዝምድና ይኖረዋል ለማለት ቃጥቶኝ አያውቅም። የ18ኛው ክፍለዘመን አበሾች ወደመቃብራቸው ሲጓዙ፣ “እኛ እንዲህ ነበርን” ለማለት ለምልክት ትተውት የሄዱት መስሎ ይሰማኛል።     

No comments:

Post a Comment