Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, July 6, 2012

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ላይ ለመወያየት ሰሞኑን ወደ ጀኔቫ አምርተው የነበሩ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ተወቀሱ

ኢሳት ዜና:- ሰኔ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ላይ ለመወያዬት ሰሞኑን ወደ ጀኔቫ  አምርተው የነበሩ የኢህአዴግ ባለስልጣናት፦“አካሄዳችሁ፤የፈራችሁትን የዓረብ ስፕሪንግ እዛው እቤታችሁ ድረስ ሰተት አድርጎ የሚያመጣ እንጂ፤መፍትሄ ሊሆናችሁ አይችልም” ተብለው ተወቀሱ።

ባለስልጣናቱ ይህ ወቀሳ የተሰነዘረባቸው፤ባለፈው ሐሙስ በስዊዘርላንድ-ጄኔቭ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ውስጥ፤ ሲቪኪዮስ -ለዜጎች ተሳትፎ ዓለማቀፋዊ ህብረት የተባለ ድርጅት-  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤን(ሰመጉ) ሪፖርት ለመስማት ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ  ነው።

በስብሰባው ላይ የጄኔቭ ነዋሪዎች፣ አምባሳደሮች  እና መቀመጫቸውን በተለያዩ አውሮፓ አገሮች ያደረጉ ድርጅቶች ተገኝተዋል። የቀድሞው ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ( ኢሰመጉ) ፤ማለትም  የአሁኑ ሰመጉ ሪፖርት በሚያሰማበት ስብሰባ ላይ ለመካፈል ወደዚያው ያቀኑ ኢትዮጵያውያን ፕሮግራሙ እስኪጀመር ድረስ በነበራቸው የግል ጨዋታ ከመካከላቸው ፦”ኢሰመጉ አሁንም አለ ወይ? ጨርሶ ያጠፉት መስሎን ነበር እኮ” የሚል ጥያቄ መሰንዘሩ ተሰምቷል።

ሌላው ተሰብሳቢ ለተሰነዘረው ጥያቄ በሰጠው ምላሽ ፦”ኢሰመጉ አሁን ሰመጉ ነው የሚባለው።ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል እንዳይጠቀሙ ተከልክለዋል።ኢትዮጵያን እስካልጨመሩ ድረስ መኖር ይችላሉ” ብሏል። የሰመጉ ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ሞላ ባቀረቡት ዝርዝር ሪፖርት፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች  በ አሳሳቢ ሁኔታ በሚፈጸምባት ኢትዮጵያ ውስጥ ድርጅታቸው በነፃ ተዘዋውሮ ለመስራት የተጋረጡበትን እንቅፋቶች አመልክተዋል።

በተለይ ከቅርብ ዓመታት በፊት የእርዳታ ድርጅቶችን አስመልክቶ ኢትዮጵያ የተገበረችው አዋጅ፤በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ  ህግጋትን በመደፍጠጥ በሥራቸው ላይ ማነቆ  መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ተናግረዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናልን በመወከል በስብሰባው የተገኙት ሚስ ክሌር ቤትሰን በበኩላቸው፤ መንግስታዊ ያልሁኑ ድርጅቶችን በሚመለከት በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግስታት ካወጧቸው ህጎች ሁሉ  እጅግ የጠበቀውን ያወጀችው ኢትዮጵያ ናት ብለዋል።

“የውጪ ድርጅት በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች አቤቱታ ማቅረብም ሆነ መዳኘት አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ የምስጢር እስር ቤቶች አሉ።ጋዜጠኞች ይታሰራሉ። የሰብዓዊ መብት ረገጣ የተለመደ ሆኗል” ሲሉም አክለዋል-ሚስ ክሌር።ኬንያዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሚስተር ማይና ኪይይ ደግሞ፦”አገራችሁ  የ አፍሪካ ኩራት ነበረች..” በማለት ነው አስተያዬት መስጠት የጀመሩት።

ሚስተር ማይና  በመቀጠልም፦”በምኒልክ አመራር የተመዘገበው የአድዋ ድል ታሪክ፤ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ መኩሪያን ተምሳሌት ነው።አፍሪካዊ በመሆኔ ታሪካችሁን እጋራለሁ።በነፃነት መቆየታችሁ፤እኛም ቀና ብለን እንድንሄድ እና ለመብታችን እንድንታገል ለመንገዳችን ብርሀን ሆኖናል።ተስፋ ሰጥቶናል” ካሉ በሁዋላ ፤”ሆኖም ላለፉት ዓመታት ስለ ኢትዮጵያ የምንሰማው ግን ምንድነው?” በማለት በሀዘን ጠይቀዋል።

ስለ ኢትዮጵያ የሚባለውን ነገር በአካል ወደዚያው አቅንተው ከሁሉም ወገኖች ጋር በመነጋገር ለማጣራት ፍላጎት ቢኖራቸውም፤ ያቀረቡት የቪዛ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ከዓመት በላይ መቆጠሩን ሚስተር ማይና ጠቁመዋል። መድረኩ ለውይይት ክፍት መሆኑን ተከትሎ የኢህአዴግ ተወካዮች በሰመጉ ሪፖርት ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል። በተለይ ጋዜጠኞች በሰበብ አስባቡ እየታሰሩ ነው የሚለውን እንደማይቀበሉ የጠቀሱት የኢህአዴግ ተወካዮች፤ጋዜጠኞች ቢታሰሩም ወንጀል ስለሠሩ እንጂ ፤ለምን ጻፋችሁ ?ተብለው አይደለም ብለዋል።

በስብሰባው የተገኙ አንዲት ኢትዮጵያዊ ለኢህአዴግ ተወካዮች በሰጡት መልስ፦”ህዝብን ማፈን የትም አያደርስም።አካሄዳችሁ፤የፈራችሁትን የዓረብ ስፕሪንግ እዛው እቤታችሁ ድረስ ሰተት አድርጎ የሚያመጣ እንጂ፤መፍትሄ ሊሆናችሁ አይችልም።የታመቀ ነገር አንድ ቀን መፈንዳቱ አይቀርም ።ከናንተ የተለየ ሀሳብ ወይም አመለካከት ያለውን ሰው በጠላትነት መፈረጁን ብትተውት ይሻላል” ሲሉ አሣስበዋቸዋል።

No comments:

Post a Comment